የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትና የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራትና የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ የዲጂታል ዕጣ ፈንታን በራስ ለመወሰንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ቴክኖሎጂን መጠቀም ብቻ ሳይሆን በራስ አቅም መፍጠር፣ ማልማት፣ መጠበቅና መቆጣጠር እንዲሁም ብቁ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ማፍራት ወሳኝ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሀሚድ ገለጹ፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር አምስተኛውን ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ሠልጣኞች አስመርቋል።
በመርሐ ግብሩ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሀሚድ እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሀሚድ በዚሁ ጊዜ፤ ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደ ዲጂታል ሥርዓት እየተሸጋገረች ባለችበት ወቅት የመንግሥት አገልግሎቶች፣ የፋይናንስ ሥርዓቶች፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ኢንዱስትሪና ትራንስፖርት በቴክኖሎጂ ላይ እየተመረኮዙ መምጣታቸው ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ዲጂታል አገልግሎቶች ሲስፋፉ የሳይበር ጥቃቶችና የመረጃ ስርቆት እየተወሳሰቡ በመምጣታቸው የሥርዓቶችን ደኅንነትና ተአማኒነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የቴክኖሎጂ ዕድገት ዋነኛ መሠረቱ የሰው ልጅ ዕውቀት፣ ፈጠራ፣ ብቃትና ቁርጠኝነት መሆኑን ተናግረው፤ የሰው ኃይል አቅም ሳይኖር የቴክኖሎጂ ግዥና አጠቃቀም ብቻ የሀገርን ዲጂታል ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደማይችል አመልክተዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የበለጸገችና በዲጂታል ኢኮኖሚ ተወዳዳሪ እንድትሆን የተቀመጠውን ራዕይ እውን ለማድረግ በስትራቴጂው ዘመን 5 ሺህ ብቁ የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎችን የማፍራት ሀገራዊ ግብ መቀመጡን ገልጸዋል።
ይህንን ግብ ማሳካት በአንድ ተቋም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ የመንግሥት ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ የምርምር ተቋማትና የሙያ ማኅበራት ሀብትና ዕውቀት በማቀናጀት መሥራት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ይህ የተቀናጀ እንቅስቃሴ የመደመር እሳቤ ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የጋራ ራዕይ፣ የአቅም መደጋገፍና ትብብርን በተግባር የሚያንጸባርቅ ሲሆን፤ የትምህርት ተቋማትን፣ የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ አቅም በማሰባሰብ ሀገራዊ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማጠናከር የሚደረግ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለት 1 ሺህ 140 ወጣቶች የአምስተኛውን ዙር ሥልጠና አጠናቀው መመረቃቸውን ጠቅሰው፤ በሥልጠናው ሂደት ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ አስተዳደሩ፣ የግሉ ዘርፍ፣ ስፖንሰሮች፣ አሰልጣኞችና ሜንተሮች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
ተመራቂዎችም የተማሩትን ዕውቀት ወደ ተግባርና ፈጠራ በመቀየር ለሀገራዊ ልማትና ደኅንነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።