የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ለቀጣናዊ ሰላምና ልማት ጉልህ አበርክቶ አለው-የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ለቀጣናዊ ሰላምና ልማት ጉልህ አበርክቶ አለው-የፖለቲካ ፓርቲዎች
ጋምቤላ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ለቀጣናዊ ሰላምና ልማት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው በጋምቤላ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባህር በር ባለቤትነት መልሳ እንድታገኝ መላው ኢትዮጵያዊያን የጀመሩት ጥረት ሁሉንም በአንድ ያሰባሰበ የጋራ አጀንዳ መሆኑንም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ በሰጥቶ መቀበል መርህና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሀገሪቱን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በአጽዕኖት ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ በጋምቤላ ክልል ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ካለው የኢኮኖሚ እድገትና ፈጣን የህዝብ ቁጥር አኳያ የባህር በር ባለቤት መሆን የህልውናና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው።
በሕዳሴ ፓርቲ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ኃላፊ መምህር ሻምበል ቶላ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ የባህር ባር ባለቤትነት ለቀጣናው ሀገራት ሰላምና ልማት ወሳኝ ሚና አለው።
ሀገሪቱ ላለፉት ዓመታት ከባህር በር ባለቤትነቷ እንድትርቅ የተደረገው በፖለቲካ ሴራ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በአሁኑ ወቅት እየተመዘገበ ካለው የኢኮኖሚ እድገትና በሀገሪቱ ካለው ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር አንፃር የባህር በር ባለቤት መሆን የሕልውና ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ በሴራና በታሪካዊ ስህተት ያጣችውን የባህር በር በሰጥቶ መቀበል መርህና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መልሳ እንድታገኝ በመደመር መንግስትና በህዝብ የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፣ የባህር በር ኢትዮጵያዊያንን ያልዩነት በአንድነት ያቆመ የጋራ አጀንዳ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የጋምቤላ ቅርንጫፍ ምክትል መሪ ኮማንደር ጋትቤል ቦል በበኩላቸው እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም ካላት ወሳኝ ሚናና ስትራቴጂካዊ የጂኦፖለቲካ አቀማመጥ አንጻር የባሕር በር ባለቤት የመሆን ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን ለቀጣናው ሰላም ካለው ፋይዳ ባለፈ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛንን ለማስጠበቅ ጭምር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የባህር በር ለማግኘት የተጀመረው ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ኮማንደር ጋትቤል፣ ይህ ጥረት ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በኢኮኖሚና በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር ለቀጣናዊ መረጋጋትና የጋራ ተጠቃሚነት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል።
የፓርቲዎቹ አመራሮች ምንም እንኳን በሚከተሉት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ልዩነት ቢኖርም በሀገርና በህዝብ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የማይናወጥ የጋራ አቋም እንዳለቸው ገልጸዋል።
በመደመር መንግስት የሀገርንና የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ሥራዎች ከመንግስት ጎን ቆመው የበኩላቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
ሀገራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና የባህር በር ጥያቄን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ሁሉም ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን እንዲወጣ በአጽንኦት ገልጸዋል።