አካል ጉዳተኞች በሀገር ግንባታ ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው-ሚኒስትር ዴኤታ ኬሪያ ኢብራሂም - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኞች በሀገር ግንባታ ንቁ ተሳታፊዎች ናቸው-ሚኒስትር ዴኤታ ኬሪያ ኢብራሂም
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦አካል ጉዳተኞች የልማት ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ በሀገር ግንባታ ንቁ ተሳታፊዎች መሆናቸውን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ኬሪያ ኢብራሂም ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህን የገለጹት 35ተኛውን አለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን አከባበር አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በዚህም አካል ጉዳተኞች የልማት ተጠቃሚዎች ብቻ ሳይሆኑ በልማት ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊና ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ዜጎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ34ኛ ጊዜ የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን ከኅዳር 25 እስከ 26 ቀን 2019 ዓ.ም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ አርባ ምንጭ ከተማ እንደሚከበር ገልጸዋል።
በዘንድሮው አከባበር የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት 20ኛ ዓመት መታሰቢያ ትኩረት እንደሚደረግበት ጠቁመው፤ ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ማጠናከርና የቀሩ ክፍተቶችን መፍታት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ተደራሽነት አካል ጉዳተኞችን ወደ መድረክ መጋበዝ ብቻ ሳይሆን፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ፣ በፍትሕና በውሳኔ ሰጪነት ሂደቶች እኩል እንዲሳተፉ ማስቻል መሆኑንም አብራርተዋል።
ተደራሽነት ለሀገራዊ ምርታማነት የሚደረግ ኢንቨስትመንት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም ሴቶችና ሕፃናት አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ከፍተኛ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች መብትና ተሳትፎ ላይ ልዩ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአካል ጉዳተኞችን እኩል ተሳትፎ ማረጋገጥ የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት እንዳልሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የፌዴራልና የክልል ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የልማት አጋሮችና ማኅበረሰቡ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው፤ የዘንድሮው በዓል የተባበሩት መንግሥታት የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት የ20 ዓመታት ጉዞ የተመዘገቡ ስኬቶችንና ተግዳሮቶችን ለመገምገም ልዩ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የመደመር መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በፖሊሲ፣ በሕግ ማዕቀፎችና በተቋማዊ አሠራሮች ማካተት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።
በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥንና የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን በማሻሻል አካል ጉዳተኞች በልማትና በውሳኔ ሰጪነት ሂደቶች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማስቻል የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ተይዟል።
ይህም የአካል ጉዳተኞችን መብት ማክበርን ከማኅበራዊ ድጋፍ ባለፈ የሀገራዊ ልማትና ምርታማነት አካል አድርጎ የማየት አካሄድን የሚያንፀባርቅ ነው።