የሳይበር ልህቀት ማዕከል እያፈራቸው ያሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎች ትልቅ ሀገራዊ አቅም ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
የሳይበር ልህቀት ማዕከል እያፈራቸው ያሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎች ትልቅ ሀገራዊ አቅም ናቸው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ የሳይበር ልህቀት ማዕከል በላቀ ዕውቀት፣ በዘመናዊ ክህሎትና በሀገር ፍቅር ስሜት እያፈራቸው ያሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎች ትልቅ ሀገራዊ አቅም መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በአምስተኛው ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ያሠለጠናቸውን ወጣቶች አስመርቋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሁሉንተናዊ የዕድገት ጉዞዋን ለማፋጠንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ነድፋ ወደ ሰፊ ትግበራ ገብታለች።
ስትራቴጂው የመንግሥት አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ማድረግ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ማረጋገጥና ዜጎችን የቴክኖሎጂ ፈጣሪና ተጠቃሚ ማድረግን ያለመ ታላቅ ሀገራዊ ራዕይ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ያለ ጠንካራ የሳይበር ደኅንነት የሚገነባ ዲጂታል መሠረተ ልማት መሠረት እንደሌለው ሕንፃ ወይም በር እንደሌለው ቤት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ዲጂታል ሥርዓቱ እየሰፋ በሄደ ቁጥር የሳይበር ደኅንነት አቅም በዚያው ልክ ካላደገ የሀገር ኢኮኖሚያዊ ጥቅምና ብሔራዊ ደኅንነት ለአደጋ እንደሚጋለጥ አሳስበዋል።
በዚህ ረገድ የሳይበር ልህቀት ማዕከሉ በላቀ ዕውቀት፣ በዘመናዊ ክህሎትና በሀገር ፍቅር ስሜት ኮትኩቶ እያፈራቸው ያሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎች የማይተካ የሰው ኃይል ግብዓት መሆናቸውን ተናግረዋል።
ተመራቂ ወጣቶቹ የክረምት ጊዜያቸውን ለጥናት፣ ለምርምርና ለሀገር ፍቅር በመስጠት ፈታኙን ሥልጠና በስኬት ማጠናቀቃቸውን ያደነቁት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ያገኙት የምስክር ወረቀት የታላቅ ሀገራዊ ተልዕኮ መጀመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ዕውቀታቸውን በሥነ ምግባር በመምራት ለሀገር ሰላም፣ ለሕዝብ ደኅንነት፣ ለተቋማት ጥበቃና ለኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲያውሉት መክረዋል።