ቀጥታ፡

የቤቶች ግንባታው የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦የቤቶች ግንባታው የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥና የከተማ ልማትን የሚያፋጥን ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የጉባ ብሥራት የሆነውን የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ የሕግ፣ የፋይናንስ እና የመሬት ዝግጅቶች ተጠናቅቀው ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል፡፡ 

ቤቶችን በፍጥነት እና በጥራት ለመገንባት የቱርኪዬ፣ የቻይና እና የኮሪያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሰፊ ጥረት መጀመሩን ጠቁመዋል።

እነዚህ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ረጃጅም ሕንፃዎችን መገንባት የሚያስችሉ ሲሆን፣ ቤቶችን በፍጥነት የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ሙከራ መጀመሩንና ወደ ሙሉ ሥራ ለማስገባት የግብአት ማስተካከያዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በመገንባት ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቅርቡ በአዲስ አበባ የተጎበኙት ቤቶች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ የመኖሪያ ቤት ችግርን የሚቀርፍ ተስፋ ሰጪ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ሚካኤል ሮባ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አመልክተዋል። 

የቤቶች ልማት ሥራዎች የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻልና ዘመናዊ የከተማ ልማትን በማፋጠን ረገድ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጡም ጠቁመዋል። 

በተጨማሪም ዘርፉ በግንባታ፣ በንግድና በተያያዥ የኢኮኖሚ መስኮች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግ አስረድተዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አብርሃም ሙሉነህ፤ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጥረት እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጸው፣ ይህም በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚኖሩ ዜጎችን የቤት ባለቤት በማድረግ ዘላቂ የኢኮኖሚ እፎይታ እንደሚያስገኝላቸው ተናግረዋል።

የቤት ባለቤት መሆን ዜጎች ዘላቂ የኢኮኖሚ ዋስትና እንዲኖራቸውና ለቤተሰባቸው የሚተርፍ ቋሚ ሀብት እንዲያፈሩ ትልቅ ዕድል እንደሚከፍት ገልጸው፣ ይህ ስኬታማ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አድንቀዋል።

ኢየሩሳሌም አበበ በበኩላቸው፣ የቤት አቅርቦት እየጨመረ መምጣቱ ዜጎች የራሳቸው መኖሪያ ቤት ባለቤት እንዲሆኑ በማስቻል ዘላቂ እፎይታና የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ዜጎች የራሳቸው መኖሪያ ቤት ባለቤት መሆናቸው ወርኃዊ ገቢያቸውን በአግባቡ እንዲቆጥቡና የቤተሰባቸውን የኑሮ ደረጃ በዘላቂነት እንዲያሻሽሉ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም