ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ ናቸው ሲሉ የዛምቢያ ጤና ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሮማ ችለንጊ ገለጹ።
በአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና በትብብር የበሽታዎች ቅኝት ላይ የተደረገውን የናይሮቢ ዲክላሬሽን መሠረት በማድረግ፤ በወረርሽኝ መከላከል ዝግጁነትና በትብብር ቅኝት ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር ያለመ የአፍሪካ የጤና ሚኒስትሮች ውይይት በአዲስ አበባ መካሔዱ ይታወሳል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የጤና ሚኒስትሮችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዛምቢያ ጤና ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሮማ ችለንጊ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብ ጤና አገልግሎትን በማስፋፋት ረገድ አስደናቂ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ተገንዝቢያለሁ ብለዋል።
በተለይ የጤና ተቋማትን አቅም ማሻሻል፣ በእናቶች ሞት ቅነሳ እና የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል ዘርፍ አዳዲስ ፈጠራዎችን በመተግበር ተጨባጭ እድገት መመዝገቡን መረዳታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የጤና ፕሮግራሞችን ራሷ በመምራት እንዲሁም የባለድርሻ አካላትን አስተዋጽኦ በአንድ ዕቅድ ሥር በማቀናጀት ረገድ የላቀ ደረጃ ላይ መድረሷን ጠቁመዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች የሀገር ውስጥ ሀብቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋሏ ተጨባጭ ለውጥ እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የጀመረቻቸው ስትራቴጂዎችም በተግባር ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ የጤና ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባከናወነቻቸው ተከታታይ የለውጥ ሥራዎች፤ በጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር አማካኝነት መሠረታዊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ለመረዳት መቻላቸውን አንስተዋል።
የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን ሥርዓትን በማስፋፋት ዜጎች የገንዘብ ጫና ሳይደርስባቸው ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉ የሚደነቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰው፤ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለትን ከማዘመን ባለፈ፣ በሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በማምረት የውጭ ጥገኝነትን ለማስቀረት እየሠራች ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን አመልክተዋል።