የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሚደርሱ ሰብሎች ልማት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሚደርሱ ሰብሎች ልማት ትኩረት ተሰጥቷል
ጂንካ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በአጭር ጊዜ ለምርት በሚደርሱ ሰብሎች ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚያስከትለውን አደጋ ቀድሞ ለመከላከል እንደ ሀገር እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ሥራዎች ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም በመደመር መንግስት የግብርና ሥራውን ከተለምዷዊ አሰራር በማውጣት ተጽዕኖን መቋቋም የሚችል የግብርና ሥርአት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመዘርጋት በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚገኙ የግብርና ምርምር ማዕከላትም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖንን መቋቋም የሚያስችሉ በሳይንሳዊ ምርምር የታገዙ የመፍትሄ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ያሲን ጎኣ (ዶ/ር) በጂንካ ምርምር ማዕከል እየተከናወኑ ያሉ የመነሻ ዘር ብዜት ሥራዎችን በተመለከቱበት ወቅት እንደገለጹት፣ የአየር ንብረት ተጽዕኖንን ተቋቁሞ ወጤታማ ለመሆን በአጭር ጊዜ ለሚደርሱ እና ድርቅን ለሚቋቋሙ ሰብሎች ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ በጂንካ፣ አርባ ምንጭ፣ አረካ፣ ይርጋጨፌ እና ሳውላ የምርምር ማዕከላት በሳይንሳዊ ምርምር የታገዘ የመነሻ ዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በምርምር ማዕከሉ ውጤታማ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማሰራጨት 469 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አመልክተዋል።
በኢንስቲትዩቱ የምግብ ሥርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኦቶሮ ኦልቄ በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በቴክኖሎጂ የታገዘ ሳይንሳዊ ምርምር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖን በዘላቂነት በመቋቋም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በኢንስቲትዩቱ ሥር የምግብ ሥርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው፣ በዚህም የምርምር ማዕከላትን አቅም በመገንባት ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ሥራ አስኪያጅና የሰብል ተመራማሪ ተክሌ ዮሴፍ (ዶ/ር)፣ የምርምር ማዕከሉ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ መቋቋም ለሚችሉና በአጭር ጊዜ ለሚደርሱ ሰብሎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በ15 ሄክታር መሬት ላይ ቦሎቄ፣ ማሾ፣ ዳጉሳ፣ ማሽላ፣ በቆሎ እና የእንሳስት መኖዎችን እያላመደ መሆኑን ተናግረዋል።
በምርምር ማዕከሉ ውጤታማ የሆኑ የሰብል ዝርያዎችንና የእንስሳት መኖዎችን ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ማዕከሉ ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በበኩላቸው፤ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖንን ለመቋቋም በዞኑ እየተሰራ ላለው ሥራ በሳይንሳዊ ምርምር የተደገፈ እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በምርምር ማዕከሉ አማካኝነት በአካባቢው የመነሻ ዘር ብዜት ሥራ መከናውኑ ቴክኖሎጂውን ለአርሶ አደሮች በቀላሉ ለማሰራጨት ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡
የዘር ብዜት ሥራው የአካባቢውን አግሮ ኢኮሎጂ ያማከለ ከመሆኑ በተጨማሪ በአርሶ አደር ማሳዎች ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም በምርምር ማዕከሉ የሚውጡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ መምሪያው አበክሮ ይሰራል ብለዋል።