ትልልቅ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገድ እንደምንችል በተግባር አሳይተናል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ትልልቅ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገድ እንደምንችል በተግባር አሳይተናል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ትልልቅ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገድ እንደምንችል በተግባር አሳይተናል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፤ እንደ ሀገራችን ሆነ፣ እንደ ከተማችን አዲስ አበባ፣ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበትን ትልቅ ኮንፈረንስ በብቃት አስተናግዳለች።
እነዚህን ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ለተከታታይ 6 ቀናት በአዳራሽ ብቻ ሳይሆን፣ በከተማችን የተለያዩ ቦታዎች እየተዟዟሩ መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል።
ቀን ብቻ ሳይሆን፣ ምሽትና ሌሊትም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በነፃነት እየተዟዟሩ ሲዝናኑ ተመልክተናል ያሉት ከንቲባዋ እነሱም ስለከተማችን ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል ብለዋል።
በዚህም ትልልቅ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገድ እንደምንችል በተግባር አሳይተናል ነው ያሉት።
ከንቲባ አዳነች ይህን ታላቅ ኮንፈረንስ ላዘጋጀው የአፍሪካ CDC ምስጋና አቅርበዋል። እንዲሁም ኮንፈረንሱን በዋናነት ላስተባበረው የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም እንግዶችን በመቀበልና በማስተናገድ፣ በትራንስፖርት፣ በሆቴል፣ በውሃ፣ በመብራት፣ በአዳራሽ አገልግሎት፣ በጸጥታ፣ በማስጎብኘት፣ በጽዳትና በሌሎችም ዘርፎች የተሳተፉ ሁሉም ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎችንም አመስግነዋል።
ይህ ስኬት አዲስ አበባ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅቶችን በብቃት፣ በጥራትና በኃላፊነት ማስተናገድ የምትችል ከተማ መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ጠቁመዋል። አዎ፣ እንችላለን! ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በብቃት አስተናግደናል፤ በሚቀጥለው ዓመትም ለCOP32 ከ100 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን በብቃትና በጥራት ለማስተናገድ እየተዘጋጀን ነው ብለዋል ከንቲባዋ በመልዕክታቸው።
ከአሁኑ ጀምሮ ልዩ ትኩረት እንስጥ፤ በእጃችን ያሉትን ሥራዎች በጊዜ፣ በጥራትና በብቃት እንፈጽም። ይህን ታላቅ እድል በምንም መልኩ ሳናባክን፣ የኢትዮጵያን የእንግዳ ተቀባይነት፣ የፈጠራ አቅምና የሥራ ትጋት ለዓለም የምናሳይበትን ታላቅ ዕድል በተግባር እናሳካ በማለት ጥሪ አቅርበዋል።
እንዲሁም COP32ን ውጤታማ፣ የማይረሳ እና የኢትዮጵያን አቅም የሚያሳይ ታላቅ ዓለም አቀፍ ዝግጅት ለማድረግ፣ ዛሬ በትጋት እንሥራ። ዓለምንም በመዲናችን እናስተናግድ፤ ኢትዮጵያንም በኩራት እናሳይ! ብለዋል፡፡