ቀጥታ፡

ኮምባይነር ተጠቅመን ሰብላችንን መሰብሰባችን ጊዜና ጉልበት ቆጥቦልናል- የወላይታ ዞን አርሶ አደሮች

ወላይታ ሶዶ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ ሰብላቸውን በኮምባይነር ታግዘው መሰብሰባቸው የምርት ብክነትን ከማስቀረት ባለፈ ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ እንዳስቻላቸው የወላይታ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ።

ከዞኑ አርሶ አደሮች መካከል በወላይታ ዞን ዳሞት ጋሌ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር መሠለ ባሳ እና ተገኔ ሙሉጌታ፤ ከባህላዊ የእርሻ ዘዴ ወደ ዘመናዊ ግብርና መሸጋገራቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል። 


 

ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር ሆነው ከ26 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ በኩታ ገጠም ያለሙትን የስንዴ ሰብል በኮምባይነር ታግዘው እየሰበሰቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የሰብል አሰባሰብ ሥራው በዘመናዊ የግብርና ማሽነሪዎች መታገዙ የምርት ብክነትን ከመከላከል ባለፈ ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ እንዳስቻላቸውም ነው የተናገሩት። 

ከስንዴ ልማት ሥራቸው በአማካይ 50 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ አርሶ አደሮቹ ጠቁመው፣ በየጊዜው ከልማቱ የሚያገኙት ምርት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በባህላዊ መንገድ ሲያከናውኑት በነበረው የእርሻ ሥራ ጊዜና ጉልበት ሲባክን እንደነበር አስታውሰው፣ "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘመናዊ የግብርና አሰራር መከተሌ እነዚህን ችግሮች አስቀርቶልኛል" ብለዋል። 


 

በኩታ ገጠም እርሻ ያመረቱትን የስንዴ ምርት በኮምባይነር ታግዘው መሰብሰብ በመጀመራቸው ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረውን የምርት ብክነት ማስቀረቱን የገለጹት ደግሞ አቶ ዘመተ ጫማ የተባሉ ሌላኛው አርሶ አደር ናቸው።

በዚህም በአንድ ሄክታር እስከ 50 ኩንታል የስንዴ ምርት እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

የወላይታ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ ምሥራቅ አብርሃም (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ ከ160 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በመኸር እርሻ ለምቷል።


 

ከዚህ ውስጥ 81 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በአዝዕርት ሰብሎች መሸፈኑን አመልክተዋል።

በመኸር ከለሙ የአዝዕርትና የሆርቲካልቸር ሰብሎችም በአጠቃላይ 16 ሚሊዮን 900 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ የመሰብሰብ ሥራው እየተፋጠነ መሆኑን ነው የገለጹት።

እስካሁንም ከ123 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ የለማ ሰብል መሰብሰቡን ጠቁመው፣ ከዚህም 13 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል።


 

የምርት አሰባሰቡ በኮምባይነር ታግዞ መከናወኑ የምርት ብክነትን ከመከላከል ባለፈ የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ እየቆጠበ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ሁሉም አካባቢዎች የኩታ ገጠም እና የሜካናይዜሽን እርሻ እየተስፋፋ መምጣት ወጤት ማስገኘቱን ምስራቅ (ዶ/ር) ገልጸው፣ በዳሞት ጋሌ ወረዳ በስምንት ስንዴ አምራች ቀበሌዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በክላስተር እንዲያለሙ መደረጉን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም