ቀጥታ፡

ከአሰራር ማነቆ ወደ ላቀ አፈጻጸም፡- የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አዲስ ምዕራፍ

አንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጤናማና ዘላቂ የሚሆነው የወጪ ንግድ አቅሙ ሲጎለብትና ከውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚገኘው ገቢ እያደገ ሲመጣ ነው።
 
የወጪ ንግድ ዘርፍ ለሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፈጠር ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
 
የመደመር መንግሥትም ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል።
 
 የዚህ የኢኮኖሚ ሪፎርም ዋነኛ ትኩረት በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የነበሩ የአሰራር ማነቆዎችን መፍታትና የሀገሪቱን የመላክ አቅም ማሳደግ ነው።
 
ለበርካታ ዓመታት ኢትዮጵያ ሰፊ የግብርና፣ የማዕድንና የኢንዱስትሪ ሀብት እያላት በአሰራር ውስንነትና በገበያ ትስስር ችግር ምክንያት ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ሳታገኝ ቆይታለች።
 
ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት በማክሮ ኢኮኖሚውና በሎጂስቲክስ አገልግሎት ላይ መሰረታዊ ማሻሻያዎችን አድርጓል።
 
በተለይም በግብርና ምርታማነት፣ በማዕድን ፍለጋና በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ለወጪ ንግድ ምርቶች በዓይነትና በመጠን መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
 
በመደመር መንግሥት አመራር ሰጪነት የተወሰዱት እነዚህ እርምጃዎች ዛሬ ላይ በተጨባጭ ቁጥሮች የሚለካ ውጤት ማስመዝገብ ጀምረዋል።

 ከዚህም ባሻገር የንግድ ሥርዓቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስተሳሰርና ለላኪዎች ምቹ የአሰራር ከባቢ መፍጠር መቻሉ የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት አሳድጎታል።
 
በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ሀብት በመቀየር በወጪ ንግድ ዘርፍ አዲስ የስኬት ምዕራፍ ከፍታለች።
 
ይህንን አበረታች የኢኮኖሚ አፈጻጸም አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ፣ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ከወጪ ንግድ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ይፋ አድርገዋል። ይህ ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ዕድገት ማሳየቱንም አብራርተዋል።
 
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ የሶስት ወር ገቢ ከሀገራዊ ሪፎርሙ በፊት ከነበሩት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ሙሉ ዓመት የወጪ ንግድ ገቢ ጋር የሚስተካከል መሆኑን አስገንዝበዋል።
 
ይህም ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እያላት ባለፉት ጊዜያት በአሰራር ውስንነት ተይዛ እንደነበር በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
በመደመር መንግሥት የተወሰዱት የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገራቸውን ይህ ውጤት ያረጋግጣል።
 
የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት የተገኘው ይህ ስኬት ተጠናክሮ በመቀጠል ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ አቅም መጎልበትና ለዘላቂ ብልጽግና መረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም