ኢጋድ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ በሚዲያ ሽልማቱ ላይ ላሳየው የላቀ የሚዲያ አጋርነት ምስጋና አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ በሚዲያ ሽልማቱ ላይ ላሳየው የላቀ የሚዲያ አጋርነት ምስጋና አቀረበ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 19/2019 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa) በዩጋንዳ ካምፓላ በተዘጋጀው የ2026 የሚዲያ ሽልማት ስነ-ስርዓት ላይ ለሰጠው የሚዲያ ሽፋንና ለነበረው የላቀ አጋርነት ልዩ ምስጋናውን አቅርቧል።
ተቋሙ ባወጣው የምስጋና መግለጫ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የሁነቱ የመገናኛ ብዙሃን አጋር በመሆን ያበረከተው ድጋፍ በቀጣናው የሚገኙ ድንቅ ጋዜጠኞችንና የዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎችን እውቅና ለመስጠት ትልቅ እገዛ ማድረጉን አመልክቷል።
እነዚህ እውቅና የተሰጣቸው ባለሙያዎች በኢጋድ ቀጣና ውስጥ ስላለው የሰዎች ነጻ እንቅስቃሴ፣ የሰራተኞች ፍልሰት፣ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም የመፈናቀል ጉዳዮችን በጥልቀት በመዘገብ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ የላቀ ስራ የሰሩ ናቸው።
ኢጋድ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የዚህ ስኬታማ ጉዞ አካል በመሆኑና በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ትኩረት የሚሹ ወሳኝ ጉዳዮችን ለዓለም ለማድረስ ለሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ጥረት ትልቅ እውቅና እንደሚሰጥ አመልክቷል።
የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (ፒኦኤ ) ጋዜጠኛ መግደላዊት ነጋ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በአየር ንብረት ለውጥ እና በግጭት ምክንያት በሚከሰት መፈናቀል ዘርፍ (Climate and Conflict-Induced Displacement) ላይ በሰራችው ፕሮግራም የ2026 የሚዲያ ሽልማት አሸናፊ መሆኗ የሚታወስ ነው።