የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ሪፎርም-የመደመር መንግሥት ስኬት ማሳያ! - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ሪፎርም-የመደመር መንግሥት ስኬት ማሳያ!
የመደመር መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተለያዩ የኢኮኖሚ እና የተቋማት ማሻሻያ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል።
የዚህ የለውጥ ጉዞ ዋና ትኩረት በሀገሪቱ የሚገኙ ግዙፍ የልማት ድርጅቶችን ከዕዳ እና ከአሰራር ማነቆ በማላቀቅ ውጤታማ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።
በተለይም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የጀርባ አጥንት እንደመሆኑ መጠን የመደመር መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶታል።
የባቡር መሰረተ ልማት ፈጣን፣ አስተማማኝ እና ወጪ ቆጣቢ የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ከፍተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የለውጡ ዋነኛ ማዕከል ሆኗል።
ይሁን እንጂ ተቋሙ ከተመሰረተበት ዓላማ አንጻር የሚጠበቅበትን ያህል ውጤት እንዳያመጣ የተለያዩ የአሰራርና የአቅም ውስንነቶች ሲፈታተኑት ቆይተዋል።
እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታትና ዘርፉን በዘመናዊ መልኩ ለማንቀሳቀስ በመደመር መንግሥት አመራር ሰጪነት በተቋሙ ውስጥ መሰረታዊ የሪፎርም ሥራዎች ተግባራዊ ተደርገዋል።
የዚህን ሪፎርም ውጤታማነት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ ኮርፖሬሽኑ በሁሉም ዘርፎች አስደናቂ ለውጥ ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
በሪፎርሙ አማካኝነት የተቋሙ ዓመታዊ ትርፍ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወደ 43 ቢሊየን ብር በማደግ ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም መፈጠሩን አንስተዋል።
ከትርፍ ዕድገቱ ባሻገር የተቋሙ የማጓጓዝ አቅምም በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል። በዚህም በዓመት ያጓጉዝ የነበረውን የመንገደኞች ቁጥር ከ198 ሺህ ወደ 588 ሺህ ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ የካርጎ ማጓጓዝ አቅሙም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።
ይህንን ሰፊ የማጓጓዝ አቅም ለማሳካት የባቡሩ የጉዞ ፍጥነት በሰዓት ከ37 ኪሎ ሜትር ወደ 55 ኪሎ ሜትር እንዲያድግ ተደርጓል።
በተጨማሪም የሎኮሞቲቮች ቁጥር ከ11 ወደ 36 እንዲሁም የጋሪዎች ብዛት ከ560 ወደ 1 ሺህ በላይ ማደጉ ለአገልግሎት ቅልጥፍናው ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።
የመደመር መንግሥት በኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ያከናወነው የሪፎርም ሥራ ተቋሙን ከኪሳራና ከዝቅተኛ አፈጻጸም በማውጣት ውጤታማ የልማት ሞተር አድርጎታል።
ይህ ስኬት ሀገራዊ የሎጂስቲክስ አቅምን ከማጠናከር ባለፈ ለቀጣይ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ትልቅ ተሞክሮ የሚሆን ነው።