ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከቀጣናው ልማትና ሠላም ተነጥሎ የሚታይ አይደለም-ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለቀጣናው ሰላም፣ ልማትና ሕልውና ካለው ፋይዳ ተነጥሎ የሚታይ አለመሆኑን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጰያ የባሕር በር ጥያቄ ከሉዓላዊነትና ከቀጣናው የኢኮኖሚ ብልጽግና ጋር የተያያዘ ስትራቴጂካዊ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

የባሕር በር ተደራሽነትን በሰላማዊና በድርድር ለማግኘት የሚደረገው ጥያቄ አዲስ አለመሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችንም አቅርበዋል።

ዮርዳኖስ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ተስማምታ በአቃባ ሰርጥ፣ ኢራቅ በፐርሺያ ባሕር ላይ፣ እንዲሁም ፖላንድ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የባሕር በር ማግኘታቸውን በማስረዳት፣ ጉዳዩን በሰላምና በመግባባት መፍታት እንደሚቻል አመልክተዋል።

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ተዘግቶባት ቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ሊሰፍንባት እንደማይችልም ነው አጽኖት ሰጥተው የተናገሩት።

በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ኢመሪተስ ፕሮፌሰርና የሕግ ባለሙያ ዓለማየሁ ገብረማርያም ለኢዜአ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ከባሕር በር እንድትርቅ የተደረገው በታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ተላላኪዎች በተቀነባበረ ሴራ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ አደገኛ ውሳኔም ኢትዮጵያን በእጅጉ ዋጋ እያስከፈላት ስለመሆኑም ነው ያብራሩት።

ኢትዮጵያ ካላት ግዙፍ ኢኮኖሚ አንጻር የባሕር በር ማግኘቷ ቀጣናውን በልማት በማስተሳሰር ዘላቂ መረጋጋት እንደሚያሰፍን አንስተው፤ በመሆኑም የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከቀጣናው ልማትና ሠላም ተነጥሎ የሚታይ አይደለም ብለዋል።

የአፍሪከ ቀንድ ቀጣና ዘላቂ ልማትና ሰላም እንዲያገኝ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ወሳኝ መሆኑን ሀገራት ሊገነዘቡ እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።

መንግስት የባሕር በር ጥያቄን ለማሳካት እየሄደበት ያለው መንገድ እጅግ የሚደነቅ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም