አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን በራሷ አቅም፣ በተቀናጀ ሥርዓትና በዘላቂ ፋይናንስ ማረጋገጥ ይገባታል - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን በራሷ አቅም፣ በተቀናጀ ሥርዓትና በዘላቂ ፋይናንስ ማረጋገጥ ይገባታል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን በራሷ አቅም፣ በተቀናጀ ሥርዓትና በዘላቂ የጤና ፋይናንስ ማረጋገጥ እንደሚገባት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) ተጠናቋል።
ጉባኤው “የአፍሪካ የጤና ደኅንነት እና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነት እና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ቀን ሁለት አህጉራዊ የጤና ስትራቴጂያዊ ፍኖተ ካርታዎች ይፋ ተደርገዋል።
የመጀመሪያው ፍኖተ ካርታ እስከ 2030 ድረስ የእናቶችን፣ ጨቅላ ሕፃናትን፣ ሕፃናትንና ወጣቶችን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ያለመ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በአፍሪካ የሚመሩ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ዲጂታል ጤና መፍትሔዎች ላይ የሚያተኩር ነው።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት፣ ባለፉት አምስት ቀናት በተካሄዱ ከ90 በላይ የውይይት መድረኮች የሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና የሲቪል ማኅበራት ተሳትፈዋል።
በዚህም አፍሪካ በአንድ ድምፅ መናገር መቻሏንና ከጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት መሸጋገር የመላው አህጉሪቱ የጋራ ግብ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተሳታፊዎች ድምፅ ግልጽና ጠንካራ እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ይህም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ በተግባር እየተከተለችው ያለው አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍና በወረርሽኞች ዝግጁነት ረገድ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን ገልጸው፣ ባለፉት ዓመታት ያገኘችውን ልምድ ለአፍሪካ ወንድሞችና እህቶች ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
አፍሪካ በዓለም አቀፉ የጤና ሥርዓት መዋቅር ማሻሻያ ሂደት ያላትን ድምፅ ማሳደግ እንደሚገባት ያሳሰቡት ዶክተር መቅደስ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራና የተቀናጀ የአፍሪካ ድምፅ እንደሚያስፈልግና ጉባኤውም ይህንን ድምፅ በሰፊው፣ በግልጽና በድፍረት ለማሰማት ዕድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ጤና በአፍሪካውያን መመራት፣ በአፍሪካውያን መደጎምና በአፍሪካውያን ጥረት መንቀሳቀስ እንዳለበት ገልጸው፣ ለዚህም ተገማች፣ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮችን የሚጠቀምና የተለያዩ የገንዘብ ምንጮችን የሚያቀናጅ የፋይናንስ ሥርዓት መከተል እንደሚገባ አመላክተዋል።
በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጃን ካሴያ በበኩላቸው፣ ጉባኤው የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የዓለማችን ትልቁ የሕዝብ ጤና ጉባኤ መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
በዘርፉ የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማላቅ ሰፊ ኢንቨስትመንት ማበረታታትና ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ያስገነዘቡት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከጥገኝነት ለመላቀቅ በራስ አቅም የሚከናወኑ ሥራዎችን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፣ አዲስ አበባ ተውባ እና ደምቃ እንግዶቿን በተገቢው መንገድ ማስተናገዷን ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት የአፍሪካ ወንድሞችና እህቶች በሕብረተሰብ ጤና ዙሪያ ለመምከር በመዲናዋ መክተማቸውን አንስተው፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን የልማትና የጤና ዘርፍ ስኬቶች በየሀገራቸው እንዲያካፍሉ እንዲሁም የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ሆነው እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።