የኢትዮጵያ የወረርሽኝ መከላከል አቅም የማኅበረሰብ ጤና ጥበቃ ሥርዓት መጎልበቱን የሚያመላክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የወረርሽኝ መከላከል አቅም የማኅበረሰብ ጤና ጥበቃ ሥርዓት መጎልበቱን የሚያመላክት ነው
አዲስ አበባ፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የወረርሽኝ መከላከል አቅም የማኅበረሰብ ጤና ጥበቃ ሥርዓት መጎልበቱን የሚያመላክት መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ ገለጹ።
ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆየውን 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) መክፈታቸው ይታወሳል።
ጉባኤውም ''የአፍሪካ የጤና ደኅንነትና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሄዷል።
በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በተዘጋጀው ጉባኤ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።
በዛሬው የጉባኤው ውሎም በአፍሪካ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ፣ የወደፊት አቅጣጫ ለወረርሽኝ ዝግጁ እና በማኅበረሰብ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መልካሙ አብቴ በዚሁ ጊዜ፤ የወረርሽኝ ሥርጭትን ለመግታት የተቀናጀ የጤና ተቋማት የቁጥጥርና መከላከል አቅም ወሳኝ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብርም ማኅበረሰብን በቅርበት የሚያገለግል የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር አቅም በመፍጠር ከፍተኛ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብርም የወረርሽኝ በሽታዎችን ቀድሞ ለመለየትና ለመቆጣጠር ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል።
የጤና ተቋማት ምላሽ ፍጥነቱም የወረርሽኝ ምልክትን በሰባት ቀናት መለየት፣ በአንድ ቀን ሪፖርት ማድረግና በሦስት ቀናት ምላሽ የመስጠት ሦስት መለኪያዎች እየተገመገሙ መሆኑን አስረድተዋል።
የማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝን ከሶስት ወራት ባነሰ ጊዜ በመቆጣጠር የተሰጠው አፋጣኝና አመርቂ ምላሽም የዝግጁነትና የጤና ተቋማትን አቅም ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ሥርዓት ዝግጁነትና አቅም ግንባታም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጭምር በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዚህ ዓመትም በድንበር አካባቢ በሚገኙና ከፍተኛ የአደጋ ተጋላጭነት ባላቸው ወረዳዎች ለበርካታ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ስልጠና በመስጠት ስምሪት መሰጠቱን ገልጸዋል።
የሙያተኞችን አቅም ግንባታ በስልጠና ማጎልበት፣ ዲጂታል የሪፖርት ሥርዓትን ማስፋፋትና ብሔራዊ የቅንጅት ሥራን ማጠናከር የቀጣይ የትኩረት መስኮች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የበሽታ መለየት፣ ማሳወቅና ምላሽ መስጠት ሂደቶች ከማኅበረሰብ እስከ ሆስፒታል ድረስ ባሉ የጤና ተቋማት በአንድ የተቀናጀ ሥርዓት መከናወን እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያም የወረርሽኝ ዝግጁነትና ምላሽ ሥርዓቷን በዚህ መርህ ላይ ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።