ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ሴሲሊያ አዱት ማንዮክ አዴንግን ዛሬ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በውይይታቸውም ሚኒስትር ጌዲዮን በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ጠንካራ ወዳጅነት አውስተው፤ የሁለትዮሽ ትብብሩን ይበልጥ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የቅርብ የሥራ ግንኙነትን ማስቀጠልና የከፍተኛ ባለሥልጣናት ጉብኝቶችን ማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
በደቡብ ሱዳን ስለሚካሄደው መጪው ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ወቅታዊ ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ የምርጫ ሂደቱን ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ሴሲሊያ አዱት ማንዮክ አዴንግ ተጠባባቂ ሚኒስትር አምባሳደር አዴንግ ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ እያበረከተች ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
ሀገራቸው ከኢትዮጵያ የሚደረግላት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት ለደቡብ ሱዳን ተማሪዎች እያደረገ ላለው የትምህርት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ተማሪዎቹ በየተሰማሩበት የሙያ መስክ ለተቋማት እያበረከቱ ያሉትን ጉልህ አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥተዋል።