ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ምርጫ ማስፈጸምን አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ምርጫ ማስፈጸምን አስመልክቶ በሀገር ዐቀፍ እና በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ዛሬ ውይይት አካሄዷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ የትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበትን ፈጣን ምርጫ ማካሄድ የፌዴራል መንግሥቱ ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሕዝቡ የተሻለውን በመምረጥ ክልሉ በተመረጡ አመራሮች እንዲተዳደርና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚገባውን ውክልና እንዲያገኝ እንደሚደረግ፣ ለዚህም የተሟላ ሰላምንና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ወደ መደበኛ ሥራ የመመለስ ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

በውይይቱ ላይ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ስኬታማ ምርጫ በቦርዱ የብቻ ጥረት የሚከናወን ተግባር ካለመሆኑም በላይ ግልጽ፣ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ተሣትፎ ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ይኸውም ከምርጫ ኦፕሬሽኑ በላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ በመሆኑ ውይይቱን ማካሄድ ማስፈለጉን ያስረዱት ሰብሳቢዋ፤ የውይይቱ ዐላማም ከባለድርሻ አካላት ግብዓት መሰብሰብ መሆኑንና ቀጣይነት እንደሚኖረው እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላትም ጋር በተመሳሳይ እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።

የሰብሳቢዋን ንግግር ተከትሎ ከተሣታፊዎቹ በርካታ ሃሳብና አስተያየት የተሰጠ ሲሆን፤ ቦርዱ ምርጫውን አስመልክቶ ውሣኔዎችን ከማሳለፉ አስቀድሞ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ለማድረግ ማቀዱ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርጫው የትግራይ ሕዝብ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር እንዲሁም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውክልና እንዲኖረው ስለሚያስችል አስፈላጊ እንደሆነም አንስተዋል።


 

በተጨማሪም በትግራይ ክልል ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውንና በተለይም በክልሉ ምርጫን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ መኖሩን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ተሳታፊዎቹ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ከተካሄደው ምርጫ ትምህርት ተወስዶ የበለጠ አፈጻጸም እንዲኖር ማስቻልም ከተሣታፊዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ ተጠቅሷል።

በውይይቱ የመዝጊያ ንግግራቸው ሜላትወርቅ ኃይሉ ለተሰጡት ግብዓቶች አመስግነው፤ የተሰጡት ሃሳብና አስተያየቶች ለምርጫው ትልቅ ግብዓት እንደሚሆኑት ገልጸዋል።

ፓርቲዎች ራሳቸውን ለምርጫው ማዘጋጀት እና ከወዲሁ ከነሱ የሚጠበቀውን ኃላፊነት ለይቶ ወደ ሥራ መግባት እንደሚያስፈልግ፤ እንዲሁም የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም ዜጎች መብታቸውን በማወቅና በመረዳት በምርጫ እንዲሣተፉ በማስተማር ረገድ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ውይይቱ በቀጣይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም