ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የመከላከያ ሚዲያ ህንፃ ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን የመከላከያ ሚዲያ ህንፃ ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በጃል ሜዳ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘውን አዲሱን የመከላከያ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ህንፃ ጎብኝተዋል።
ጥር ወር 2017 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ህንፃ በያዝነው ወር መጨረሻ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ አጠቃላይ የህንፃውን የግንባታ ሂደት በተመለከተም ፕሮጀክቱ በሚመለከታቸው አመራሮች እና የሥራ ተቋራጮች አማካኝነት ገለፃ ተደርጓል።
የሚዲያ ህንፃ ግንባታው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አሁንም ድረስ አሥፈላጊውን ሙያዊ የማማከር እና ሌሎች ድጋፎችን እያደረጉ ለሚገኙት ለኢዜአ እና ለሌሎች የሚዲያ ቴክኖሎጂ ሙያተኞች እና ተቋማቱ በዕለቱ ምስጋና ተችሯቸዋል።
ይህ ዘመናዊ የሚዲያ ህንፃ መገንባቱ በቀጣይ ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖር ከማድረጉም ባሻገር የተቋሙ ሚዲያ በአራቱም ሚዲየሞች ቀን ከሌሊት ያለማቋረጥ ታማኝ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ለመሥራት ታሳቢ ተደርጎ እየተገነባ ያለ ሲሆን ግንባታው በያዝነው ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል።
የፕሮጀክት ተቆጣጣሪ መሃንዲስ ኢንጂነር አዳም በቀለ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ባለሶስት ወለል የሚዲያ ህንፃ አምስት ዘመናዊ ስቱዲዮዎችን ጨምሮ አንድ ዘመናዊ የሚዲያ ተቋም ሊኖረው የሚገባውን ክፍሎች እና አደረጃጀቶች የያዘ ሆኖ መገንባቱን አሥረድተዋል።
ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚመራው የመከላከያ ጠቅላላ አገልግሎት ማዕከል ሲሆን፣ የኘሮጀክቱ አማካሪ ደግሞ የመከላከያ ኮንስትራክሽን እና ዲዛይን ድርጅት ነው።