ቀጥታ፡

መከላከያ ሠራዊት- የቀጣናው ወንድም ሕዝቦች አስተማማኝ የሠላም ዋስትና

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በታሪክ፣ በባህልና በደም የተሳሰረ በመሆኑ፣ የዲፕሎማሲ ፖሊሲዋ "ጎረቤትን ማዕከል ያደረገ" እንዲሆን አድርጎታል።

የአንድ ሀገር ሰላምና ብልጽግና ከጎረቤቶቿ ሰላምና መረጋጋት ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ኢትዮጵያ በጽኑ ታምናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም ራሷን እንደታላቅ ወንድም በመቁጠር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በረጅሙ የሀገርነት ታሪኳ የራሷን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አስከብራ በመኖር ረገድ አኩሪ ታሪክ ያላት ቢሆንም፤ የሌላውን ሀገር ድንበር ጥሳና ወርራ ግን ፈጽሞ አታውቅም።

ይልቁንም የኢትዮጵያ ታሪክ የሚመሰክረው፣ በጎረቤት ሀገራት ላይ የሰላም መደፍረስና የህልውና ስጋት በተጋረጠ ቁጥር ቀድማ በመድረስ አለኝታነቷን በተግባር ማሳየቷን ነው።


 

ከጎረቤቶቿም አልፋ ከኮሪያ እስከ ኮንጎ፣ ከሩዋንዳ እስከ ላይቤሪያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ የኢትዮጵያ ሰራዊት የከፈለው የህይወት ዋጋ የዚህ የማይናወጥ የሰላም ወዳድነት አቋም ህያው ምስክር ነው።

በጎረቤት ሀገራትም ከዳርፉር እስከ አብዬ፣ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በሶማሊያ በጀግንነቱና በዲሲፕሊኑ የሚታወቀውን መከላከያ ሰራዊቷን በማሰማራት የጎረቤት ወንድም ሕዝቦች አለኝታ ሆናለች።

የኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊት መገንባት መሰረታዊ ዓላማ የማንንም ሉዓላዊነት መጋፋት ሳይሆን፣ ለራሷ ህዝብና ለወንድም የቀጣናው ህዝቦች ሰላምና ደህንነት አስተማማኝ ዋስትና መሆን ነው።

ጠንካራ ሰራዊት መኖር ለሽብርተኝነትና ለቀጣናዊ አለመረጋጋት የሚሆኑ ሃይሎች መፈንጫ እንዳይሆን ትልቅ ጋሻ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ሰራዊቷን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በእውቀትና በስነ-ምግባር ስትገነባ የቆየችውም የአፍሪካ ቀንድ የሰላምና የልማት ቀጣና እንዲሆን ካላት ጽኑ ፍላጎት የተነሳ ነው።

ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ተቋማቷን በላቀ ደረጃ እያዘመነችና እያጠናከረች የምትገኘው ለዚሁ ትልቅ ዓላማ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትናንትናው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ በሰጡት ማብራሪያም ይህንኑ ዕውነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

በቅርቡ የታጠቀቻቸው የአየር ኃይል ዘመናዊ ትጥቆችም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከማስከበር ባለፈ፣ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ዘብ ለመሆን ያላትን አቅም ይበልጥ የሚያጎለብቱና ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶችን በጋራ ለመመከት የሚያግዙ እንደሆኑ አመላክተዋል።


 

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የታገዘ የመከላከያ ሰራዊት፣ ለጎረቤት ሀገራት ስጋት ሳይሆን ታላቅ አለኝታና መከታ ነው።

እየተገነቡ ያሉት ዘመናዊ የመከላከያ ተቋማት፣ የማሰልጠኛ ማዕከላትና የቴክኖሎጂ አቅሞች ኢትዮጵያን ከማንኛውም ጥቃት ከመከላከል ባለፈ፣ ለጎረቤት ሀገራት ደህንነት ዘብ የሚቆሙ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ተጠንቀቅ ሻለቆቿን በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከማሰማራት ባሻገር የቀጣናው ሀገራትን ወታደራዊ መኮንኖች በማሰልጠንም ሌላ ደማቅ አሻራ አሳርፋለች።

በቀጣናው የሚከሰቱ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን፣ ጽንፈኝነትንና የሰላም ጠንቆችን በጋራ ለመመከት የኢትዮጵያ የመከላከያ አቅም ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

የኢትዮጵያ የመከላከያ ግንባታና የውጭ ዲፕሎማሲ አንዱ ሌላውን የሚደግፉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው።

ጎረቤትን ያስቀደመ ዲፕሎማሲዋ የጋራ ልማትንና ትስስርን ሲያፋጥን፣ ጠንካራ የመከላከያ ተቋሟ ደግሞ ይህ የጋራ ልማትና ሰላም እንዳይደናቀፍ ዋስትና ይሰጣል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች የሕይወት ምንጭ የሆኑ ወንዞቿን ብቻ ሳይሆን፣ የማይናወጥ ሰላምና መረጋጋትን በማበርከት ረገድ የማይተካ ታሪካዊ ሚና እየተወጣች ትገኛለች።

የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከግጭትና ከሽብር ስጋት ነፃ ሆኖ የጋራ ልማትን እንዲያረጋግጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ከፍተኛ ነው።


 

የሰራዊቱ መጠናከር የቀጣናውን የጋራ ደህንነት የሚያስጠብቅ፣ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና የሽብር ጥቃቶችን የሚመክት ጠንካራ ጋሻ ነው።

በታሪክ እንደታየውም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዎች ሕይወቱን ገብሮ ሰላምን ያስከበረ፣ ለወንድም ሕዝቦች ደህንነት ሲል መስዋዕትነት ከፍሏል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የሚመሰከርለት ከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊን፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ሰብዓዊ ክብር የተላበሰ ሰራዊት ነው።

በተሰማራበት ቀጣና ሁሉ የአካባቢውን ሕዝብ ባህልና እሴት የሚያከብር፣ ንፁሐንን ከጥቃት የሚታደግና የወንድማማችነትን መንፈስ የሚያጠናክር መሆኑ ለጎረቤት ሀገራት ዜጎች ፍጹም የደህንነት ዋስትና ይሰጣል።

ጠንካራዋ ኢትዮጵያና የዘመነው የመከላከያ ሰራዊቷ ለምስራቅ አፍሪካ ሕዝቦች የጋራ ብልጽግና፣ የዘላቂ ሰላምና የአንድነት ምሰሶ ሆነው ይቀጥላሉ።

ኢትዮጵያ ትናንትም፣ ዛሬም ሆነ ነገ የቀጣናው የሰላም አምባሳደርና የጎረቤቶቿ የማይነቃነቅ አለኝታ ሆና ትቀጥላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም