ቀጥታ፡

አፍሪካ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ፈጣሪና ላኪ ለመሆን በሀገር በቀል እውቀት ላይ ማተኮር ይገባታል

ባህርዳር፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦አፍሪካ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተጠቃሚ ብቻ ሳትሆን ፈጣሪና ላኪ ለመሆን በሀገር በቀል እውቀት ላይ በማተኮር መስራት እንደሚገባት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ገለጹ።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ 8ኛውን ዓለም አቀፍ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ልማት ጉባኤ እያካሄደ ነው።


 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ አገራት የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት በምርምር ላይ የተመሰረተ የቴክኖሎጂ ማመንጨት፣ ማስፋፋትና መጠቀም ላይ ማተኮር ይገባል።

ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ኃይል በማፍራት ለዘርፉ እድገት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው አሳስበዋል። 

ይህም አፍሪካ የዲጂታል ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የሚያስችል እውቀትን በራሷ ማመንጨት፣ ቴክኖሎጂን ለመፍጠርና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችላት መሆኑን አስረድተዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የምርምር ማዕከል በማቋቋም፣ በርካታ የሰው ኃይል በማፍራት፣ በሥልጠናና በቴክኖሎጂ ሽግግር አበረታች ውጤት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል። 

ጉባኤውም ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን የያዘውን ግብ ለማሳካት የልምድ መለዋወጫና አዳዲስ እውቀቶችን ለማመንጨት የሚያስችል መድረክ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ሙሉቀን ዘገየ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጉባኤው የአፍሪካ ተመራማሪዎች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘንድሮው ጉባኤ ላይም በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሳይበር ደህንነት (ሳይበር ሴኩሪቲ)፣ በዲጂታላይዜሽንና በሌሎች ተያያዥ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ የጥናት ሥራዎች መቅረባቸውን አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው መምህር የሆኑት አቶ በላይነህ ተሾመ እንደገለጹት፤ በትራፊክ አደጋ ትንበያና ቅድመ ግምት ላይ ያካሄዱትን ምርምር በጉባኤው ላይ አቅርበዋል።

ምርምሩ የትራፊክ አደጋ መረጃን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ታግዞ በመተንተን የአደጋ አዝማሚያንና ቅድመ ትንበያን በማስቀመጥ መፍትሔ ለማበጀት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ከአገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች በተጨማሪ የአፍሪካና የሌሎች አህጉራት የዘርፉ ምሁራን በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም