ቀጥታ፡

የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ የአህጉሪቷን የጤና ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የተወሰደበት ነው 

አዲስ አበባ፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ የአህጉሪቷን የጤና ሉዓላዊነት ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ ግንዛቤ የተወሰደበት መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኅዳር 14 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል 5ኛውን ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡

በአፍሪካ ሲዲሲ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በተዘጋጀው በዚህ መድረክ፣ የአፍሪካን የጤና ሉዓላዊነትና ጽናት ለማረጋገጥ ከ100 ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። 


 

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው እንደገለጹት፣ ጉባኤው የአፍሪካን የጤና መረጃ ሥርዓት በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሰው ሰራሽ አስተውሎት በማዘመን ዙሪያ ሰፊ ውይይት እያደረገ ነው። 

በተጨማሪም በሀገር ውስጥ የመድኃኒትና የሕክምና ግብዓቶችን ምርት በማሳደግ የውጭ ጥገኝነትን መቀነስ ሌላው የጉባኤው አቢይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስረድተዋል።  

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው የሚመጡ የጤና ሥጋቶችን ቀድሞ ለመከላከልና ለመቋቋም የሚያስችሉ ስልቶችም በመድረኩ በስፋት ተዳስሰዋል። 

ለዚህም ኢትዮጵያ የጤና፣ የግብርናና የአካባቢ ጥበቃ ተቋማትን በማቀናጀት፣ በሰውና በእንስሳት ጤና ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን አስቀድሞ በመለየት ፈጣን ምላሽ የመስጠት ሥራ እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።

የሕክምናና የሕዝብ ጤና ግብዓቶችን ከውጭ ከማስመጣት ይልቅ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማሳደግ የጤና ዘርፉ ዋነኛ ትኩረት ሲሆን፣ መንግሥትም አምራቾችን የሚያበረታቱ የድጋፍ ፖሊሲዎችን እየተገበረ ይገኛል ብለዋል። 

የተለየ የመድኃኒት ማምረቻ የኢንዱስትሪ ማዕከል መኖሩ፣ ለሀገር ውስጥ ምርቶች የግዥ ቅድሚያ የሚሰጥ ሕጋዊ አሠራር እንዲሁም የውጭ ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚሰጡ ማበረታቻዎች የዚሁ ጥረት ማሳያዎች ናቸው ብለዋል። 

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ግብዓቶች የውጭ ገበያንም እንዲደርሱ ለማድረግ የቀዝቃዛ ሰንሰለት መሠረተ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል። 

በተጨማሪም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰፊ ዓለም አቀፍ በረራዎች ምርቶችን ወደ ሌሎች ሀገራት በቀላሉ ለማድረስ የሚያስችሉ ጠቃሚ አቅሞች ናቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም