የዓድዋን የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ገድል የበለፀገች ሀገር በመገንባት ልንደግመው ይገባል - ከንቲባ አብዱላሂ አደም - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋን የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ገድል የበለፀገች ሀገር በመገንባት ልንደግመው ይገባል - ከንቲባ አብዱላሂ አደም
ድሬደዋ፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የዓድዋን የህብረ-ብሔራዊ አንድነት ገድል የበለፀገች ሀገር በመገንባት ልንደግመው ይገባል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አብዱላሂ አደም ገለጹ።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ማጠቃለያ ዛሬ አክብሯል።
ከንቲባ አብዱላሂ አደም በወቅቱ እንደገለጹት፤ በየዓመቱ የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የሕዝቦችን ትስስርና አንድነት ይበልጥ በማጠናከር፣ ዜጎች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል።
በዓሉ የብዝኃነት ውበት፣ የአንድነት ጥንካሬና የጋራ እሴቶች ይበልጥ የሚጠናከሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ቀደምት ጀግኖች አባቶቻችን በህብረብሔራዊ አንድነት ለሀገር ነፃነትና ሉዓላዊነት የፈጸሙትን ገድል ተምሳሌት በማድረግ፣ የበለፀገች ሀገር ለትውልድ ለማስረከብ በቁርጠኝነት የምንረባረብበት ወቅት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ጫልቱ ሁሴን በበኩላቸው፤ የዘንድሮው የ21ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል መሪ ቃል ብዝኃነት ለሀገር አንድነት፣ ለጋራ ልማትና ለፍትሐዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ያለውን ወሳኝ ሚና የሚያንጸባርቅ ነው ብለዋል።
አክለውም እነዚህን ሀገራዊ ግቦች በተቀናጀ ርብርብ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መትጋት እንደሚገባ የሚያስገነዝብ መሆኑን አመልክተዋል።
በምክር ቤቱ አዘጋጅነት በተለያዩ ሁነቶች ሲከበር ቆይቶ ዛሬ በሲምፖዚየም የተጠቃለለው በዓሉ፤ የሕገ-መንግስትና የፌዴራሊዝም አስተምህሮዎችን ይበልጥ በማስረጽ፣ የብዝኃነት ውበትንና ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት ወሳኝ መደላድል የፈጠረ መሆኑንም አፈጉባዔዋ ገልጸዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተሳተፉት የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳና ዑጋዞች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ነዋሪዎች፤ ለሀገርና ለድሬዳዋ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ የበኩላቸውን ድርሻ ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።