ቀጥታ፡

በክልሉ የሻይ ቅጠል ልማትን በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው

ቦንጋ፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሻይ ቅጠል ልማትን በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን አስታወቀ።

በመደመር መንግስት ትኩረት የተሰጠው የሻይ ቅጠል ኢኒሼቲቭ በኢትዮጵያ የሻይ ምርትን በስፋትና በጥራት በማልማት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማሳደግ እና የአረንጓዴ ልማት ግቦችን የመደገፍ ግብ ይዞ እየተተገበረ ይገኛል።

እንደሀገር ለሻይ ቅጠል ልማት ምቹ ስነ ምህዳር ካላቸው አካባቢዎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አንዱ ነው።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ፣ የሻይ ቅጠል ለክልሉ ስትራቴጂክ ተክል መሆኑን ጠቅሰው በካፋ እና ሸካ ዞኖች በስፋት እየለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ልማቱ ለሀገር የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ ሥነምህዳርን የሚጠብቅ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረና አሲዳማ አፈር ላይ የሚበቅል በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በክልሉ በልማት ድርጅቶችና በአርሶ አደሮች በ2ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ የሻይ ቅጠል መልማቱን አንስተው፣ በአሁኑ ወቅት ልማቱን ለማስፋፋት በስድስት ወረዳዎች የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ አምስት ዓመታት የሻይ ቅጠል ልማትን በማስፋፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ መታቀዱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።


 

በተያዘው በጀት ዓመትም ተጨማሪ 112 ሄክታር መሬት በሻይ ቅጠል ለማልማት ታቅዶ ወደተግባር መገባቱንና ለዚህም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

እንደ አቶ አስራት ገለጻ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች የምርት አቅርቦት መጠን ከነበረበት በ17 ነጥብ 5 በመቶ ማሳደግ የተቻለ ሲሆን ዘንድሮም 7 ሺህ 200 ቶን የሻይ ቅጠል ምርት ለገበያ ለማቅረብ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በካፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ውሽውሽ ቀበሌ ላለፉት ዓመታት በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮችም በልማቱ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።


 

የሚቺቲ ሻይ ቅጠል አምራች አርሶ አደሮች ሕብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ አርሶ አደር እንግዳ መሐመድ እንደገለጹት፣ በስድስት አርሶ አደሮች የተጀመረው የሻይ ልማት በአሁኑ ወቅት 178 አባላትን በማቀፍ ተጠቃሚ እያደረገ ነው።

በማህበሩ በ216 ሄክታር መሬት ላይ የሚያመርቱትን የሻይ ቅጠል ምርት ለውሽውሽ ሻይ ልማት እንደሚያቀርቡ ገልጸው፣ ሻይ ቅጠል ተገቢ እንክብካቤ ከተደረገለት በዓመት እስከ 6 ዙር ምርት ይሰጣል ብለዋል።

አማራጭ ገበያ እንዲፈጠርላቸውና የማሽን ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠየቁት አቶ እንግዳ፣ ዘርፉ ከሌሎች የግብርና ሥራዎች የተሻለ ጥቅም ስለሚያስገኝ በቀጣይ በስፋት እንደሚያለሙ ገልፀዋል።


 

የዩኒዬኑ አባል አርሶ አደር ከድር እንድሪስ በ2005 ዓ.ም የሻይ ቅጠል ልማት ሥራ እንደጀመሩ ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም በሁለት ሄክታር መሬት ላይ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

በተሰጣቸው ትምህርት መሠረት በሦስት ሄክታር ማሳ ላይ የሻይ ቅጠል ማልማታቸው የተናገሩት አርሶ አደር ይማም አሊ በበኩላቸው፣ ለልማቱ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሰራ የተሻለ ጥቅም ይገኝበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም