በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ121 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከ121 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተዘራ ሰብል ተሰብስቧል
ባህር ዳር፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት ከ121 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተዘራ ሰብል መሰብሰቡን የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ አንዷለም አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዞኑ ለወጪ ንግድና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ምርቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ይገኛል።
በመኸር የምርት ዘመኑም ከ151 ሺህ 900 ሄክታር በላይ መሬት ላይ ለኤክስፖርትና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ ሰብሎች የለሙ ሲሆን፣ ከአራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በተደረገ ጥረትም እስካሁን ከ121 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የለማ ሰብል መሰብሰቡን ገልጸዋል።
ከተሰበሰበው ሰብል መካከል አኩሪ አተር፣ ለውዝ፣ ስንዴና ኑግ ይገኙበታል ነው ያሉት።
የሰብል አሰባሰቡ እየተካሄደ የሚገኘውም አርሶ አደሩን በልማት ቡድን በማደራጀትና በደቦ የመስራት ባህልን በመጠቀም መሆኑን አቶ አንዷለም ተናግረዋል።
በዞኑ በጃዊ ወረዳ የአይማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አለማየሁ አለኸኝ እንደገለጹት፣ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ከዘሩት የለውዝና የአኩሪ አተር ሰብል ከ70 ኩንታል በላይ ምርት ይጠብቃሉ።
ሰብሉ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ባደረጉት ጥረት የለውዝ ሰብላቸውን ሰብስበው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ የአኩሪ አተሩን ምርት በማጨድና በመውቃት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በዚሁ ወረዳ የኩራንድ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አታላይ መለሰ በበኩላቸው፣ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የዘሩትን የለውዝና የአኩሪ አተር ሰብል ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር እየሰበሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ በአጠቃላይ 412 ሺህ 480 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 17 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያስረዳል።