በክልሉ ዘላቂነት ያለው የስራ እድል በመፍጠር የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ዘላቂነት ያለው የስራ እድል በመፍጠር የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ዘላቂ የስራ እድል በመፍጠር የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ስራ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።
ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት የማጠቃለያ ፕሮግራም በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል፡፡
የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ በመድረኩ እንደተናገሩት፤ ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ አግባብ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በተለየ ትኩረት እየተሰራ ነው።
ለዚህም ወደ ሥራ የሚገቡ ወጣቶችን አመለካከት፣ ክህሎትና ዕውቀት በማሳደግ የላቀ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ወደ ሥራ ለሚገቡ ወጣቶች የመሥሪያ ቦታ እና ካፒታል የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት በአጭር ጊዜ ሀብት ማፍራት እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ ከ10 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር በማመቻቸት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ለሚልቁ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ሥራ በቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን አቶ አማረ ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም ከ410 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች ደረጃውን የጠበቀ ሥልጠና በመስጠት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የአማራ ክልል አስተባባሪ አቶ ይበልጣል አያሌው በበኩላቸው፤ ለሥራ አጥ ወጣቶች ሥልጠናዎችን በመስጠት እና ከፋይናንስ ተቋማት ጋር እንዲተሳሰሩ በማድረግ ረገድ ስኬታማ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተደረገ ጥረትም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ማመቻቸት መቻሉን ነው የገለጹት።
ከ180 ሺህ በላይ ወጣቶችም መደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
ወጣት ክንዴ ንጉሤ፤ «ሶሉሽን ኢንጂነሪንግ» የተሰኘ ድርጅት በማቋቋም በጥናትና ምርምር እንዲሁም ለኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ማሽኖችን በማምረት ሥራ ላይ መሰማራቱን ነው የገለጸው።
በአሁኑ ወቅትም ለ15 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሶ፤ በንፋስ ኃይል የሚሰሩና ለመኖ ማቀነባበሪያ የሚያገለግሉ ማሽኖችን በማምረት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግሯል።