ቀጥታ፡

ከፋፋይ ትርክቶችን በመከላከል ለሀገራዊ አንድነት የበኩላችንን እንወጣለን-የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች 

ሚዛን አማን፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ከፋፋይ ትርክቶችን በመከላከልና የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም መጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ የቤንች ሸኮ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። 

በዞኑ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች 21ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን "በብዝኃነት የደመቀች፤ በምክክር የጸናች ስልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ ኩነቶች አክብረዋል።

ነዋሪዎቹ በመደመር መንግስት ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ጠብቆ ባህልን የማልማት ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፣ በኅብረ ብሔራዊነት የደመቀው ኢትዮጵያዊ ማንነት በአብሮነት እሴት ጸንቶ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ለዘመናት የዘለቁ የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል። 


 

ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኬሜቶ ኬቶ ለኢዜአ እንዳሉት፣ የተዛቡ ትርክቶች ዜጎች እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ የራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅት በመደመር እሳቤ የተዛቡ ትርክቶችን ለማረምና የወል ትርክትን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

በአብሮነት መቆም ለኢትዮጵያውያን ጌጥና ጠላትን ድል ማድረጊያ ኃይል ነው ያሉት አቶ ኬሜቶ፣ እርስ በእርስ ተከባብሮ የመኖር የቆየ እሴታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

የአብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም መጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።


 

መምህር ደነቀ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያን በብዙ መንገድ የተጋመደ ማንነት ያለን በመሆኑ በከፋፋይ ሀሳብና ትርክቶች እርስ በእርስ መነጣጠል እንደማይገባ ጠቅሰዋል።

ሰላምና መከባበርን በማጎልበት በወንድማማችነት መንፈስ በአንድነት መኖር ለኢትዮጵያ ዕድገትና ከፍታ ጠቃሚ እንደሆነም ተናግረዋል።

ወይዘሮ አማረች ቸርነት የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ፤ የመደመር መንግሥት የተደበቁ ባህላዊ እሴቶች ይበልጥ አደባባይ እንዲወጡና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ገልጸው፣ ይህም የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶችና ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ አድርጓል ብለዋል።


 

የቀኑ መከበር በሕገ መንግሥቱ ለእኩልነትና ለባህል ልማት የተሰጠውን መብት በተግባር ለማረጋገጥ እያገዘ በመሆኑ አብሮነትን በማጎልበት ለሀገራዊ አንድነትና ልማት በጋራ እንቆማለን ብለዋል።

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኮጁ በዳካች፤ በዞኑ ልዩነትን እንደ ውበት በመጠቀም በሕብረ ብሔራዊነት የደመቀ የልማትና ሰላም ግንባታ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የቆየውን የአብሮነትና የመተባበር እሴት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የገለጹት አስተዳዳሪው፣ ልዩነትን እንደ ጸጋና ውበት ተቀብሎ ለአንድነቱ የሚጸና ትውልድ ግንባታ ላይ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በሕዝብ ተሳትፎ የተጀመሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ውጥኖችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም