ኢትዮጵያ በዲጂታል ጤናና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ አርዓያ የሚሆኑ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዲጂታል ጤናና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ አርዓያ የሚሆኑ ውጤታማ ተግባራትን አከናውናለች
አዲስ አበባ፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በዲጂታል ጤናና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ አርዓያ የሚሆኑ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኗን የሩዋንዳ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢቫን ቡተራ ገለጹ።
5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ሲሆን፤ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የሩዋንዳ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢቫን ቡተራ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ጉባኤው በጤና ደኅንነት፣ በጤና ሉዓላዊነት፣ በዲጂታል ጤናና በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዙሪያ መምከሩ እጅግ ተገቢ ነው።
በአፍሪካ ሀገራት በዘርፉ ከፍተኛ ዕድገት እየታየ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያም በዲጂታል ጤናና በሰው ሠራሽ አስተውሎት መስክ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኗን አድንቀዋል።
በመሆኑም ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት እርስ በርስ በመተባበር ይህንን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለአፍሪካውያን አገልግሎትና ተጠቃሚነት ማዋል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ውብና አረንጓዴ መሆኗን አንስተው ንጹህ አካባቢና ተስማሚ የአየር ንብረት ለሰው ልጅ ጤና ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት እያከናወነች ያለውን ጥረት አድንቀው ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።
ሩዋንዳ የማኅበረሰብ ጤና ሠራተኞች በስማርት ስልኮች መረጃ ከመሰብሰብ ጀምሮ ጤና ጣቢያዎችንና ሆስፒታሎችን በማስተሳሰር ሙሉ የጤና ዘርፏን ዲጂታል ማድረጓን በጉባኤው ላይ ልምዷን ማካፈሏን ዶክተር ኢቫን ገልጸዋል።
በዚህ ሥርዓት ውስጥ የአፍሪካ ወጣቶች ተሰጥኦና ክህሎት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ኢቫን፣ አህጉሪቱ በአፍሪካና ለአፍሪካ በሚል መርሕ የራሷን የጤና መረጃ በራሷ የመምራት ሙሉ አቅም እንዳላት አመልክተዋል።
በመሆኑም የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን ሀብት፣ ተሰጥኦና ፍላጎት በመጠቀም እርስ በርስ በመማማርና በትብብር በመሥራት አህጉሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።