በጅማ ከተማ ባለፉት አራት ወራት ከ 700 በላይ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ ገብተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ከተማ ባለፉት አራት ወራት ከ 700 በላይ ኢንተርፕራይዞች ወደ ስራ ገብተዋል
ጅማ፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ) በጅማ ከተማ ባለፉት አራት ወራት ለ702 ኢንተርፕራይዞች አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን የከተማዋ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል ወጣቶችን በማደራጀት፣ የመሥሪያ ቦታ፣ የሊዝ ማሽንና የብድር አቅርቦት በማመቻቸት የሥራ ዕድል መፍጠርና የሥራ አጥነትን መቀነስ በዋና የትኩረት አቅጣጫነት ተይዞ እየተከናወነ ይገኛል።
በተለይ በግብርና ምርቶች እሴት መጨመር እንዲሁም በእንስሳትና ዶሮ እርባታ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍና የገበያ ትስስር በመፍጠር የአካባቢውን ምርት ተወዳዳሪ ማድረግና የወጣቶችን ገቢ ማሳደግ የልማት ጥረቱ አካል ነው።
በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን በጅማ ከተማ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት የስራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ አሸናፊ ግርማ ለኢዜአ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ በነዚህ ኢንተርፕራይዞች እስካሁን ለ4 ሺህ 582 ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል።
መንግሥት የመሥሪያ ቦታ እና የብድር አቅርቦትን ማመቻቸትን ጨምሮ የኢንተርፕራይዝና ሌሎች አጫጭር ሥልጠናዎች ቀደም ብለው መሰጠታቸውን አብራርተዋል።
ወደ ስራ የገቡት 702 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁት ደግሞ በኢንዱስትሪ፣ በከብትና በዶሮ እርባታ እንዲሁም በሌሎች የተለያዩ የሥራ መስኮች መሆኑን አክለዋል።
በዚህም ለ212 ማኅበራት ጠንካራ የገበያ ትስስር የተፈጠረ ሲሆን፣ ቀሪዎቹንም የመደገፍ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
የጅማ ከተማ ነዋሪዋ ሲቲና ሁሴንና ጓደኞቻቸው ቀደም ሲል በሥራ አጥነት ሲቸገሩ ቢቆዩም፣ በዚህ ዓመት ከከተማ አስተዳደሩ ባገኙት ድጋፍ የበቆሎ ዱቄት ፋብሪካ በመክፈት ወደ ሥራ ገብተዋል።
ሲቲናና ጓደኞቻቸው አራት ሆነው በመደራጀት የጀመሩት ይህ ሥራ ለ15 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
መንግስት ባመቻቸላቸው የሊዝ ማሽንና የመሥሪያ ቦታ በአሁኑ ወቅት ሥራቸውን በትጋት እያከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ ሰፊ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውና ምርታቸውን ከጅማ ከተማ ባሻገር ለሌሎች አካባቢዎችም ለማቅረብ እየሠሩ መሆኑን አክለዋል።
በፋብሪካው የሥራ ዕድል ካገኙ ወጣቶች መካከል ረኢስ ጣሂርና ሚስራ ነጋሽ ይገኙበታል።
ወጣቶቹ በመደራጀት የሚጀምሯቸው መሰል ፋብሪካዎች ለሌሎችም ተስፋ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከሚያገኙት ገቢ ቤተሰቦቻቸውን እየደገፉ መሆኑን ተናግረዋል።