ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን የበለጸገ ባህል፣ የዘመናት ታሪክና ብዝኃነት በዘመናዊ የፊልም ጥበብ ለዓለም የማስተዋወቅ ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የበለጸገ ባህል፣ የዘመናት ታሪክና ብዝኃነት በዘመናዊ የፊልም ጥበብ ለዓለም የማስተዋወቅ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ገለጹ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአርክዉድ ኢንተርቴይመንት አክሲዮን ማኅበር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 2ኛው የአርክዉድ አፍሪካ የፊልም ገበያና ሽልማት (AAFMA 2026) ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ መንግሥት የፈጠራ ኢኮኖሚውን ለማጎልበትና የኪነ-ጥበብ ዘርፉ ለሀገር ዕድገት ያለውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የፖሊሲና የዕቅድ ዝግጅት በማጠናቀቅ እየሠራ ይገኛል።

ዘርፉ የሀገርን ገጽታ ለመገንባትና ታሪክን በራስ ድምፅ ለመተረክ ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

የአርክዉድ ኢንተርቴይመንት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አርሴማ ወርቁ በበኩሏ፤ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ያለው መድረክ የባለሙያዎችን ክህሎትና አቅም በመገንባት ላይ ያተኮረ ነው ብላለች፡፡

በዚህም ከብሪቲሽ ካውንስል ጋር በመተባበር የአራት ቀናት የአልባሳት ዲዛይን ሥልጠና መሰጠቱን አመልክተው፤ ፌስቲቫሉን በየዓመቱ በማጠናከር በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ የፊልም ገበያ ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የብሪታኒያ ምክትል አምባሳደር ሉክ ባሎክ በበኩላቸው፤ ብሪታኒያ የፊልም ኢንዱስትሪውን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ለማስተሳሰርና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሠራ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከ120 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ የፊልም ታሪክና የበለጸገ ባህል ያላት መሆኗን የጠቀሱት ምክትል አምባሳደሩ፤ ዘርፉ የሴቶችንና የወጣቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለውን አቅም በማድነቅ የብሪታኒያ መንግሥትና ብሪቲሽ ካውንስል ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካን የኦዲዮ ቪዥዋል ኢንዱስትሪ ሥርዓት መገንባት፤ ከአቅም ወደ ተግባር በሚል መሪ ሐሳብ ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ፣ የአህጉሪቱ የፊልም ባለሙያዎች ከዓለም አቀፍ ባለሀብቶችና አሠራጮች ጋር ትስስር እንደሚፈጥሩ ተገልጿል።

በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ ባለሀብቶች እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትና ከአፍሪካ ውጭ የመጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም