የጉባ ብስራት የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ አዲሱን የመደመር ሥልጣኔ የመቅረጽ ግዙፍ አቅም አላቸው - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የጉባ ብስራት የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ አዲሱን የመደመር ሥልጣኔ የመቅረጽ ግዙፍ አቅም አላቸው - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
አዲስ አበባ፤ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የጉባ ብስራት የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ አዲሱን የመደመር ሥልጣኔ የመቅረጽ ግዙፍ አቅም እንዳላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው፣ "ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ራእይ" በሚል መርሕ የሚከናወኑት የጉባ ብስራቶች የኢትዮጵያን የመቻል አቅም ማሳያና የዕድገት መሻትን የሚተልሙ ግዙፍ የልማት ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ፣ የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ልማት፣ የኒውክሌር ኃይልና የጎዴ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
በሶማሌ ክልል የሚገኘው የኦጋዴን የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ለሀገር ውስጥ የሴራሚክስ ፋብሪካዎችና ለአዲስ አበባ የከተማ አውቶቡሶች ግብዓት በመሆን እያገለገለ መሆኑን አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በዘመናዊ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በመታገዝ እየተገነባ መሆኑንና የመጀመሪያው የቦታ መረጣ ተጠናቅቆ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ ግንባታ ጨረታ በሂደት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የጎዴ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ 18 ሺህ የሚጠጉ የሠራተኛ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በከፍተኛ ክትትል እየተገነባ መሆኑን እንዲሁም በ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ልማት መርሐ ግብር የዜጎችን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ዘመናዊ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በጉዳዩ ላይ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ የኢትዮጵያ ዋነኛ የዕድገት አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት መካከል አቶ አዲስ ዓለምአየሁ እንደገለጹት፣ ግዙፍ ፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜ በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ መድረሳቸው የሚደነቅና ለመጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የማስረከብ ራእይን የሚያሳኩ ናቸው።
ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ አብዮት ደለለኝ በበኩላቸው፣ የፕሮጀክቶቹ የ24 ሰዓት (24/7) የግንባታ ውጤታማነት የኢትዮጵያን ጀምሮ የመፈጸም ብቃት የገለጠ ታሪካዊ የሥራ ባህል መሆኑን አንስተው፣ አዲሱን የመደመር ሥልጣኔ የመቅረጽ ግዙፍ ኃይል እንዳላቸው አስረድተዋል።
የምክር ቤቱ አባል አቶ ሳምሶን ወንድሜነህ እንዳሉትም፣ የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራእይ በስትራቴጂካዊ የልማት ትልም እየሰመረ መጥቷል።
የምክር ቤቱ አባላት አክለውም፣ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና ጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የሚጠበቅባቸውን የክትትል፣ የድጋፍና የቁጥጥር ኃላፊነት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።