ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የአዳዲስና የነባር መንገዶች ግንባታና ጥገና ስራ እየካሄደ ነው

ባህር ዳር፤ ህዳር 16/2019 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ እና  የነባር መንገዶች ማጠናቀቂያና የጥገና ሥራ መጀመሩን የክልሉ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፋሲል ድልነሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የመንገድ ተደራሽነትን በማስፋፋት የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል እየተሠራ ይገኛል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ በጀት የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ፣ የነባር መንገዶች ጥገና  ሥራ  መጀመሩን ገልጸዋል። 

ከዚህ ውስጥ የክልሉ መንግሥት በመደበው ወደ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት የ120 ኪሎ ሜትር አዳዲስ መንገዶች ፣ የ32 የመንገድ ስትራክቸሮችና ድልድዮች ግንባታ ተጀምሯል ብለዋል።

የመንገዶቹ ግንባታ
በዋግ ኽምራ ዞን፣ በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር እንዲሁም በሌሎች ዞኖች መሆኑን እየተካሔደ መሆኑን አመልክተዋል።

የመንገዶቹና የድልድዮቹ መገንባት ወረዳን ከወረዳ፣ ቀበሌን ከቀበሌና ከዋና መስመር በማገናኘት የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል።

ከፌዴራል መንገድ ፈንድ ጽሕፈት ቤት በተገኘ ከ1 ቢሊዮን 376 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ደግሞ  የ6 ሺህ 85 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶች ጥገና ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። 

በመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራውም በአካባቢው ለሚገኙ በርካታ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደተፈጠረ  ጠቁመው ፤ ሥራው በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወን ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት የ90 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር አዲስ መንገድ ግንባታና የ5 ሺህ 613 ኪሎ ሜትር ነባር መንገዶች ጥገና ሥራ ማከናወን መቻሉን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም