ቀጥታ፡

በምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ከ12 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ተዘጋጅቷል

ጭሮ፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ኦሮሚያ ዞን ባለፉት ወራት ከ12 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በኦሮሚያ ክልል የአፈር ለምነትን በዘላቂነት ለማሻሻልና ለኬሚካል ማዳበሪያ የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ከብስባሽ ማፋጠኛ ቴክኖሎጂዎች ጋር ተቀናጅቶ በዞኖች ደረጃ በንቅናቄ እየተስፋፋ ይገኛል።

በክልሉ በሚገኙ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እና በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው የሚገኙ የሰብልና የእንስሳት ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጁና እንዲጠቀሙ ሰፊ የክህሎትና የግንዛቤ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት በዋናነት በበጋ መስኖ ልማት፣ በበልግና በመኸር እርሻ ወቅቶች የሚካሄዱ የሰብል ልማት መርሐ ግብሮችን በግብዓት ለመደገፍ ታስቦ ይከናወናል።

የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈርን ለምነትና እርጥበት የመያዝ አቅም ከማጎልበት ባለፈ፣ የግብርና ምርትን ወጪ ቆጣቢና ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችል መሠረታዊ የልማት አቅጣጫ ነው። 

የምስራቅ ኦሮሚያ ዞን የልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አህመድ አቡበከር ለኢዜአ እንደገለጹት ከተፈጥሮ ማዳበሪያው አብዛኛው በጥቅምት ወር ውስጥ በተካሄደ የአርሶአደሮች ንቅናቄ የተዘጋጀ ነው።

አርሶ አደሮች በአካባቢያቸው የሚገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጁ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ሰፊ የንቅናቄ ሥራ ሲካሄድ ቆይቷል።

በባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል አርሶ አደሮች በንቃት በመሳተፋቸው ከ12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀቱንና ይህም ከዓመታዊ ዕቅዱ በ100 ሺህ ሜትር ኪዩብ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።

አርሶ አደሮች ካዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በተጨማሪ ከ250 ሺህ ኩንታል በላይ ቨርም ኮምፖስት ማዘጋጀታቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።

በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ንቅናቄው የዞኑ 36 ወረዳዎች 100 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን አቶ አህመድ ጠቁመዋል።

የተዘጋጀው የተፈጥሮ ማዳበሪያ በበጋ መስኖ፣ በበልግና በመኸር እርሻ ወቅቶች ከ800 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ማልማት እንደሚያስችልም ኃላፊው አስታውቀዋል።

ይህም በአርሶ አደሩ የምርት ወጪ ላይ እፎይታ ከመፍጠሩም በላይ የአፈርን ጥራትና ለምነት በማሻሻል ለተሻለ ምርታማነት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቁሟል።

ከተፈጠረው ልምድና ተሞክሮ አንጻር በዞኑ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ላይ የአርሶ አደሮች ግንዛቤና ተነሳሽነት እየጨመረ መምጣቱን አቶ አህመድ ገልጸዋል።

በዚህም ሁሉም አርሶ አደር በአካባቢው የሚገኙ ግብአቶችን በአግባቡ በመጠቀም ማዳበሪያውን በራሱ አዘጋጅቶ እንዲጠቀም የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች በሰፊው እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

 የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ ጥቅም ላይ ማዋል የኬሚካል ማዳበሪያ ወጪን በመቀነስና የአፈር ለምነትን በማሻሻል የሚኖረውን ፋይዳ በተመለከተ በግብርና ባለሙያዎች ያልተቋረጠ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም