በሐረር ከተማ የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚያሳልጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረር ከተማ የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚያሳልጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ነው
ሐረር፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ በሐረር ከተማ የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚያሳልጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ገለጸ።
የአስፓልት መንገዱ ግንባታ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የመደመር መንግስት ለከተሞች ልማትና እድገት መፋጠን ሰፋፊ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የህዝብን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ይገኛል።
በተለይም ለመሰረተ ልማት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጦ ከመተው ይልቅ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ ተገንብተው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ እያደረገም ይገኛል።
በከተሞች ከሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መካከል መንገድ አንዱ ሲሆን በተለይም በከተሞች ለሚከናወኑ የቱሪዝም፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲሳለጡ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
በሐረር ከተማም ከኮሪደር ልማቱ ጋር በተያያ የተገነቡት የአስፓልት መንገዶች የከተማዋ ውበት ይበልጥ እንዲጎላ እያደረጉ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብትና የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሳልጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ በተፋጠነ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል።
የክልሉ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሃላፊ ኢንጅነር ፈርሃን ዚያድ እንደገለጹት፤ በክልሉ በተያዘው የበጀት ዓመት እየተካሄደ ያለው የአስፓልት መንገድ ከ11 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን ነው።
የአስፓልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱ ከእግረኛ መንገድ በተጨማሪ የመብራት፣ የፍሳሽ መስመር እና ሌሎች አስፈላጊ የመሰረተ ልማቶችን አሟልቶ እየተገነባ ይገኛልም ብለዋል።
የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራውን በታቀደለት ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል፡፡
የመንገዱ መገንባት የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ከማሳለጥ ባለፈ ሐረርን ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ ያደርጋታል ብለዋል።
በከተማው እየተገነባ የሚገኘው የአስፓልት መንገድ በአካባቢው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ተግባራት ላይ መነቃቃት መፍጠር መቻሉን የገለጹት ደግሞ በከተማው አሚር ኑር ወረዳ ገንደ ፌሮ ቀበሌ ነዋሪ መሀመድ ዩስፍ ናቸው።
ሌላው የቀበሌው ነዋሪ ደሜሳ ኡመር በበኩሉ የአስፓልት መንገዱ ግንባታ መንግስት ለህዝቡ የልማት ስራዎችን በትኩረት እያከናወነ መሆኑን የሚያሳይና የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብሏል።
የአስፓልት መንገድ ግንባታው የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን የሚያሰፋና ለነዋሪው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት አስለዲን አብዱልሰቡር ነው።