ቀጥታ፡

የአፍሪካን የውስጥ አቅም በማጎልበት የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራትን የውስጥ አቅም በማጎልበት የሕዝብ ጤና ጥበቃ የአደጋ ምላሽ ዝግጁነት ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኅዳር 14 እስከ 18 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ የሚቆየውን 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ (CPHIA 2026) መክፈታቸው ይታወሳል።

ጉባኤውም ''የአፍሪካ የጤና ደኅንነትና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።

በአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል እና በኢትዮጵያ መንግሥት ትብብር በተዘጋጀው ጉባኤ ከ100 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ታድመዋል።

የጉባኤው ተሳታፊዎች ለኢዜአ እንዳሉትም፣ አፍሪካ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ሉዓላዊነቷን የሚያረጋግጥ የራስ አቅምና ሥርዓት መገንባት ይጠበቅባታል።

የጉባኤው ተሳታፊ በዩጋንዳ የምባራራ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ረዳት መምህር ዶክተር ፒተር ክሪስኮጌዝ፣ አፍሪካ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ጥገኝነትን ማስወገድ የሚያስችል አቅም አላት ብለዋል።

ለዚህም የአህጉሪቷን ዜጎች የጤና ተጋላጭነትና ድንገተኛ የወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት የሚያጎለብት የሰው ሀብት ልማትና የራስ አቅም፣ የሕክምና ግብዓት ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት መድኃኒትና የሕክምና ግብዓት ማምረት መጀመሩም የአፍሪካን የሕዝብ ጤና ሉዓላዊነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ሁነኛ ምልክት እንደሆነ ተናግረዋል።

የማላዊ የሕዝብ ጤና ተቋም ባልደረባ ግሬስ ፉንሳኒ በበኩላቸው፣ ድንገተኛ በሽታና ወረርሽኝ ድንበር ተሻጋሪ በመሆናቸው አህጉራዊ ትብብርና ቅንጅትን ማጎልበት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአፍሪካውያንን የበሽታና ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ተጋላጭነት መግታት የሚያስችል የትብብርና ራስን የመቻል የውስጥ የመከላከልና መቆጣጠር አቅም መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከቃል የተሻገረ ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ ናይጄሪያዊው የብሉም ፐብሊክ ሄልዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር ቺሜዚ ኦገስቲን አንያኮራ ናቸው።

5ኛው ዓለም አቀፍ የሕዝብ ጤና ጉባኤም አህጉራዊ የጤና ሥርዓትን ማሻሻል የሚያስችል የጋራ ድምጽ በማስተጋባት የቀጣይ ተግባራዊ እርምጃ እያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም