በሌማት ትሩፋት የወተት ልማት ሥራ መሰማራታችን ገቢና ተጠቃሚነታችንን አሳድጓል-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በሌማት ትሩፋት የወተት ልማት ሥራ መሰማራታችን ገቢና ተጠቃሚነታችንን አሳድጓል-አርሶ አደሮች
ሀዋሳ፤ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ ተጠቅመው በዘመናዊ የወተት ልማት ሥራ የተሰማሩ የሲዳማ ክልል ወንዶ ገነት ወረዳ አርሶ አደሮች ገቢና ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገለጹ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ ከተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ትኩረቶች መካከል የወተት ልማት አንዱ ሲሆን፣ በዘርፉ የተገኘው ምርታማነት የዜጎችን ገቢ እያሳደገ ይገኛል።
በወንዶ ገነት ወረዳ ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች እንደገለጹት፣ የሀገረሰብ ላሞችን በተሻሻሉ ዝርያዎች በመተካታቸው በምርታማነታቸው ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል።
ከአርሶ አደሮቹ መካከል አቶ ተስፋዬ ዋታ ባገኙት ሥልጠና መሠረት በአንድ የተሻሻለ የወተት ላም የጀመሩትን ሥራ አሁን ወደ 15 ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።
በቀን እስከ 120 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብም ልጆቻቸውን ከማስተማር ባለፈ የቤተሰባቸውን ሕይወት መቀየር መቻላቸውን ገልጸዋል።
ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ አሰለፈች አሰፋ በበኩላቸው፣ በቀን ከሁለት ሊትር በላይ የማይሰጡ የሀገረሰብ ላሞችን በተሻሻሉ ዝርያዎች በመተካታቸው በአሁኑ ወቅት 20 የወተት ላሞች ባለቤት መሆናቸውን አስረድተዋል።
የተሻሻሉ ላሞች ተገቢ እንክብካቤ ከተደረገላቸው በቀን እስከ 20 ሊትር ወተት እንደሚሰጡ ጠቅሰው፣ በሥራቸው ለአምስት ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
የወንዶ ገነት ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ይብራ፣ በወረዳው የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ 48 የወተት መንደሮች ተደራጅተው ከዝርያ ማሻሻል ጎን ለጎን የእንስሳት ጤናና የመኖ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አደገ ዓለሙ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በክልሉ የወተት ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በዘንድሮው ዓመት ከ310 ሺህ በላይ ላሞችን ዝርያ ለማሻሻልና ከ830 ሺህ ቶን በላይ ወተት ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው።