ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባለፈ ኢትዮጵያን የዓለም አቀፍ ትኩረት አድርጓል-የዘርፉ ባለሙያዎች

ሚዛን አማን፤ ሕዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ያስመዘገበችው ስኬት የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ጥቅምና ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ማስገኘቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

ባለፉት ዓመታት በመርሐ ግብሩ የተተከሉ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የተሯቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ እድርገዋል።

እንዲሁም የምግብ ችግኞች ምርታማነታቸው እንዲጨምር ከማስቻላቸውም በላይ፣ በማኅበር ለተደራጁ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና ደን ትምህርት መምህር ተስፋዬ ቶሎሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማትና በታዳሽ ኃይል አጠቃቀም ያስመዘገበቻቸው የሚለኩ ውጤቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ፊት አውራሪ እንድትሆን አድርጓታል።

ይህ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ተጨባጭ ውጤት ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን የማዘጋጀት ዕድል እንድታገኝ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይህም ከካርበን ሽያጭና ከአየር ንብረት ጥበቃ ተጨማሪ ገቢ እንድታገኝ አስቻይ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ደን፣አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ለማ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዜጎች ተፈጥሮን የመጠበቅ ባህል እንዲያዳብሩ ማድረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ የደን ሀብት ጥበቃን ከልማት ጋር በማስተሳሰር በተከናወኑ ሥራዎችም የማር፣የቅመማ ቅመምና የሌሎች የግብርና ምርቶች ምርታማነት እየሰፋ መምጣቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ባለሙያዎቹ አክለውም፣ የአረንጓዴ አሻራን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የበለጠ ለማሳደግ የነበረውን የደን ሀብት በመጠበቅ አዳዲስ ተከላዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም