በሸገር ከተማ በሩብ ዓመቱ እስካሁን ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ በሩብ ዓመቱ እስካሁን ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ሸገር፣ህዳር 18/2019 (ኢዜአ)፦ የሸገር ከተማ አስተዳደር በ2019 በጀት ዓመት ባከናወነው ተግባር በሩብ አመቱ ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የከተማው ገቢዎች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ አበው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ሸገር ወጪውን በራስ አቅም ለመሸፈን በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ፣ከማዘጋጃ ቤታዊ እና ከውስጥ ገቢ በድምሩ 65 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ወደ ሥራ ገብቷል።
በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሶስት ወራት በተከናወነው ቅንጅታዊ ሥራም ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ግብርን ለከተማውና ለሀገር ልማት፣ለማኅበራዊ አገልግሎት እና ለዴሞክራሲ ግንባታ መሠረት መሆኑን ተገንዝቦ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተከታታይ ውይይቶችና ሥልጠናዎች ተካሂደዋል ብለዋል።
በተጨማሪም የገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን ግብር ከፋዮች ወደ ጽሕፈት ቤት ሳይመላለሱ ባሉበት ሆነው ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ መደረጉ መጉላላትንና ብልሹ አሠራርን ከመቀነስ ባለፈ የክፍያ ሂደቱን ግልጽና ፍትሐዊ አድርጎታል ነው ያሉት።
በተለይም በተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ዙሪያ በተሰጠው ሰፊ ግንዛቤ፣ ትልልቅ ግብር ከፋዮችና ለቫት የተመዘገቡ አካላት ሕጋዊ ደረሰኝ እንዲቆርጡ በመደረጉ የተሻለ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
በሌላ በኩል ሕገ-ወጥነትን ለመከላከልና የገቢ ምንጮችን ለማስፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት በተደረገ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ፣ ሕጋዊ ደረሰኝ ያልቆረጡና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ያደረጉ 400 ነጋዴዎች እንዲቀጡ ተደርጓል ብለዋል።