የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማት አቅም ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት ጠንካራ መሠረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማት አቅም ለአፍሪካ የጤና ሥርዓት ጠንካራ መሠረት ነው
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17/ 2019(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልና የአረንጓዴ ልማት አቅም ለአፍሪካ የዲጂታል ጤና ሥርዓት ጠንካራ መሠረት መሆኑን በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሆንግሶከ ኮ ገለጹ።
''በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገሩ የጤና ሥርዓቶችን ማሳደግ፤ ዲጂታል የጤና ቴክኖሎጂንና ቀጣናዊ ትብብርን መጠቀም''በሚል መሪ ሐሳብ ቀጣናዊ ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት አምባሳደር ሆንግሶከ ኮ፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይልና በአረንጓዴ ልማት ለአፍሪካ የዲጂታል ጤና ሥርዓትና ለአረንጓዴ ሽግግር መሠረት ናት ብለዋል።
የዓለም የጤና ድርጅትን መረጃ ዋቢ በማድረግም በአፍሪካ ከሚከሰቱ የሕዝብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ወባን፣ ኮሌራንና ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል በሰው ሠራሽ አስተውሎት የታገዙ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የወረርሽኝ ትንበያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የአየር ንብረትና የጤና ቀውሶች ድንበር የማይገድባቸው በመሆኑ የጋራ የበሽታ ክትትልን፣ የአገራትን ባለቤትነትና የመረጃ ሉዓላዊነትን የሚያከብር ድንበር ተሻጋሪ የጤና መረጃ አጠቃቀም ሥርዓት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ኮሪያ በዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ፋውንዴሽኗ (KOFIH) እና በሁለትዮሽ ትብብር የጤና ሥርዓቶችን ለማጠናከር የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር የማኅበረሰብ ተሳትፎና መሠረታዊ የጤና እንክብካቤ መሪ ሥራ አስፈጻሚ እስራኤል አታሮ በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ጥበቃና የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የጤና ሥርዓትን በማጠናከር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
ጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤ ላይ የተመሠረተ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።