በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚጠበቅብንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚጠበቅብንን እንወጣለን
አዲስ አበባ፤ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የቀረቡ ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚጠበቅብንን ድርሻ በቁርጠኝነት እንወጣለን ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ማብራሪያቸው፤ መንግሥት የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለውም አረጋግጠዋል።
በምክክሩ 4 ሺህ ተመካካሪዎች በአንድ ቦታ ምክክር ማድረጋቸው በራሱ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸው፤ ሂደቱ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል የለወጠና መሠረት የጣለ መሆኑን አንስተዋል።
ምክረ ሐሳቦቹ በፖሊሲ፣ በአሠራርና በሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጭምር የሚመለሱ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት መንግሥት ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለው ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አዲስ ዓለምአየሁ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምክክሩ አሳታፊና የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ የወከለ ነው።
ምክክሩ የኢትዮጵያን ችግሮች ከመሠረቱ የምንፈታበት፣ አለመግባባቶችን ማረም የምንችልበት፣ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ልዕልና ቁልፍ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ቀጣይ የቤት ሥራችን ምክረ ሐሳቦቹን ወደ ተግባር ለመቀየር መትጋት መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት የምክክር ጉባኤውን ምክረ ሐሳቦች ሳይሸራረፉ ለመተግበር ቁርጠኝነት መኖሩን አረጋግጠዋል ብለዋል።
ምክረ ሐሳቦቹን ገቢራዊ በማድረግ ሂደት የምክር ቤት አባላት ሚና ቁልፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሕዝብ የጣለባቸውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሌላዋ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አብዮት ደለለኝ በበኩላቸው፤ ሕዝቡ የምክረ ሐሳቦቹን ትግበራ በጉጉት የሚጠብቀው መሆኑን ገልጸዋል።
ምክረ ሐሳቡ የሕዝብን ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲተገበር ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል።
አለመግባባትን በኃይል ሳይሆን በውይይት መፍታት ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ መሆኑን ምክክሩ ተጨባጭ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዶክተር እሸቱ ገብረማሪያም ናቸው።
ምክክር ለሰላምና ለዕድገት ሁነኛ መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፤ የዚህ ታሪካዊ ሂደት አካል በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል፤ ለምክረ ሐሳቦቹ ትግበራ የድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል።