ኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅሟን በማሳደግ ለአገራዊ ልማት በስፋት ለማዋል እየሠራች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅሟን በማሳደግ ለአገራዊ ልማት በስፋት ለማዋል እየሠራች ነው
አዲስ አበባ፣ህዳር 17/ 2019 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላትን አቅም በማሳደግ ለዘላቂ አገራዊ ልማት በስፋት ለማዋል እየሠራች መሆኑን የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአፍሪካን የሕዋ ሳይንስ ፖሊሲ አቅም፣ ትብብርና አህጉራዊ አመራር ለማጠናከር ያለመው ሁለተኛው «አዲስ ስፔስ ፎረም 2026» በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩትና በአፍሪካ ስፔስ ሳይንስ አመራር ኢንስቲትዩት (ASLI) በጋራ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
ዶ/ር የሽሩን በፎረሙ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የሕዋ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂን ለዘላቂ ልማት በማዋል ረገድ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
ኢንስቲትዩቱ የኢትዮጵያን የመጀመሪያና ሁለተኛ የምድር ምልከታ ሳተላይቶች «ኢቲአርኤስኤስ-1» (ETRSS-1) እና «ኢቲ-ስማርት አርኤስኤስ» (ET-Smart-RSS) በቅደም ተከተል ማልማቱን ጠቅሰው፤ ሦስተኛ የምድር ምልከታና የመገናኛ ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የሳተላይት መረጃዎችን ለግብርና፣ ለከተማ ፕላን፣ ለአደጋ ቅድመ ማስጠንቀቂያ፣ ለተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ጥናትና ለብሔራዊ ደኅንነት ለማዋል እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የራሷ ሳተላይቶች መኖራቸው በምትፈልገው ጊዜና የጥራት ደረጃ የምድር ምልከታ መረጃዎችን እንድታገኝ ከማስቻሉም በላይ በሳተላይት ልማትና በምህንድስና ዘርፎች የአገር ውስጥ አቅምን ለመገንባት እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
የአፍሪካ ስፔስ አመራር ኢንስቲትዩት (ASLI) መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኤቲም ኦፊኦንግ በበኩላቸው፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የሕዋ ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ላይ ያላትን ተጽዕኖ ለማጠናከር በሳይንቲስቶችና በዲፕሎማቶች መካከል ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወሰኑ የሕዋ ጉዳዮች ሁሉንም አገራት የሚመለከቱ በመሆናቸው በሳይንስና በዲፕሎማሲ ማኅበረሰቦች መካከል ቀጣይነት ያለው ቅንጅት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረትንና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽንን ጨምሮ ዋና ዋና ተቋማትን ማስተናገዷ ለአህጉሪቱ የሕዋ ዲፕሎማሲ አስፈላጊ ማዕከል እንድትሆን ማስቻሏንም ጠቁመዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) የጂኦ-ስፔሻል መረጃ አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አንድሬ ኖንጉየርማ በበኩላቸው፤ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በአህጉራዊ ደረጃ የሚከናወኑ የሕዋ ሳይንስ ተግባራትን ከዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎች ጋር በማስተሳሰር የአፍሪካ ድምፅ በዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲሰማ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በተጨማሪም አፍሪካ በሕዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላትን አቅም ለማሳደግ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር የትብብርና የአጋርነት ዕድሎችን ለማስፋት ኮሚሽኑ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።