ቀጥታ፡

21ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በድምቀት ለማክበር ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል

ጅማ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦ 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን በስኬት ለማክበር ሰፊ እና ሁሉን አቀፍ ዝግጅት መደረጉን የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ጠሃ ቀመር ገለጹ።

ከንቲባው አቶ ጠሃ ቀመር በዛሬዉ ዕለት ለበዓሉ ስኬታማነት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ስልጠና ከወሰዱ ወጣቶች ጋር ውይይት አድርገዋል።


 

ከንቲባው በወቅቱ እንዳሉት፣ ጅማን ተመራጭና ግዙፍ የንግድና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ፣ ለመጪው ትውልድ የምትመች፣ ዘመናዊና ውብ ከተማ አድርጎ ለመገንባት ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

እነዚህ የመሠረተ ልማትና የከተማ ማስዋብ ሥራዎችም የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል ባሻገር፣ የከተማዋን ሁለንተናዊ እድገትና ተወዳዳሪነት ይበልጥ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን አንስተዋል።

በተለይም በኮሪደር ልማትና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብሮች ከተማዋን ውብና ማራኪ በማድረግ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓልን በውቢቷ እና ኅብረ-ብሔራዊቷ ጅማ ከተማ በታላቅ ፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት መንፈስ ለማክበር ሰፊ እና ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ታሪካዊቷና ውቢቷ ጅማ እንግዶቿን በታላቅ ፍቅር ተቀብላ በደመቀ ኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባህልና ወግ ለማስተናገድ ከወጣቶቿ ጋር በመሆን ዝግጅቷን ሙሉ በሙሉ አጠናቃለች ብለዋል።

የከተማዋ ወጣቶችም በላቀ መነሳሳት፣ በፍቅርና በአብሮነት መንፈስ እንግዶችን በክብር ለመቀበልና የከተማዋን ውበትና መልካም ገጽታ ለማሳየት ሁለንተናዊ ዝግጅታቸውን አጠናቀው በጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ ብለዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የጅማ ከተማ ወጣቶች ሊግ ኃላፊ አቶ ሙተሲም ሀጂረሻድ፣ በዓሉ በደመቀ ሁኔታና በስኬት እንዲጠናቀቅ 1 ሺህ 300 ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥልጠና ወስደው ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ወጣቶች እንግዶችን በክብር በመቀበል፣ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ በማስጠበቅ እንዲሁም የተለያዩ የእንግዳ ተቀባይነትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በመስጠት የበዓሉ ድምቀትና ስኬት አካል ሆነው እንደሚያገለግሉ አረጋግጠዋል።

በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ ወጣቶቹ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት እየሠሩ ከመሆናቸውም በላይ የጽዳት፣ የደም ልገሳ እና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች መካከል የጅማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወጣት ሂክማ ከድር እና ወጣት ሙነወር አባኦሊ፣ ለበዓሉ ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን በታላቅ ፍቅር፣ በንቃትና በኢትዮጵያዊ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ተቀብለው ለማስተናገድ የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እንግዶች ያለምንም መስተጓጎል የሚፈልጉትን አገልግሎት በቀላሉ እንዲያገኙ መረጃ በመጠቆምና በማመቻቸት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።


 

በጅማ ከተማ የተከናወነው የኮሪደር ልማትና የታሪካዊ ቅርሶች እድሳት፣ ከተማዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ የጋራ ታሪክን በጥልቀት ለማወቅና ለመረዳት የሚያስችል ትልቅ ዕድል መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ ወጣት ኪያ ኤፍሬም እና ወጣት አሚና አባራያ ናቸው።   

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእርስ በርስ ወንድማማችነትን ከማጠናከር ባሻገር ሰፊ የባህል ልውውጥ ለማድረግ የሚረዳ ታላቅ መድረክ በመሆኑ፣ ለበዓሉ በስኬት መጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ በንቃት እንደሚወጡም ወጣቶቹ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም