ቀጥታ፡

የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የህዝቦችን ወንድማማችነትና አንድነት አጎልብቷል

ሃዋሳ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የህዝቦችን ወንድማማችነትና አንድነት በማጎልበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት እንዲገነባ ማስቻሉን የሲዳማ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ  እመቤት ኢሳያስ ገለጹ።

የክልሉ ምክር ቤት 21ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት አካሂዷል።


 

የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ እመቤት ኢሳያስ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀን በዓል ህገ መንግስቱንና የፌዴራሊዝም ሥርአቱን መሰረት በማድረግ የሚከበር ነው። 

የፌዴራሊዝም ሥርአቱ የህዝቦችን ወንድማማችነትና አንድነት በማጎልበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዓሉ በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች በተለያዩ ሁነቶች መከበሩን ያነሱት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፣ ዛሬ በክልል ደረጃ የሚከበረው በዓል በፌደራሊዝም ጽንሰ ሃሳብና በተገኙ ጠቀሜታዎች ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር ያለውን ፋይዳ ለማጉላት ከተለያዩ ክልሎች ተወካዮች ጋር በአብሮነት እያከበሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በክልሉ የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት እንደሚያስችል ገልጸዋል።


 

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የወላይታ ዞን ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ተሰማ ኡቱላ በበኩላቸው፤ የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖር መሰረት የጣለ ነው ብለዋል።

የሲዳማና የወላይታ ህዝቦች የጋራ ማንነት ያላቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ለሀገራዊ አንድነትና ለጋራ ብልጽግና በትብብር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የሲዳማ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ በሪሁን በራሳ በበኩላቸው የቀኑ መከበር በልዩነት ውስጥ ያለውን ውበት አጉልቶ ለማውጣት የሚያስችል ነው።

በተጨማሪም በዓሉ ለብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ እድገት ጉልህ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው በወንድማማችነት ስሜት ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የውይይት መድረኩ "በብዝሃነት የደመቀች፤ በምክክር የጸናች ስልጡን ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደ ሲሆን በፌደራሊዝም ጽንሰ ሃሳብና ባስገኛቸው ጥቅሞች ላይ ያተኮረ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም