ቀጥታ፡

የመከላከያ ሰራዊት ለቀጣናዊ ሰላምና ደህንነት ድጋፍ ማድረግ የሚያስችለውን አቅምና ዝግጁነት እያሳደገ  ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቀጣናው የሚገኙ ሀገራትን ሰላምና በደህንነት ማስጠበቅ ረገድ ድጋፍ ማድረግ በሚያስችለውን አቅምና ዝግጁነት እያጠናከረ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በመገኘት ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ የመከላከያ ሰራዊት የቀጣናውን የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታ መለየትና ማወቅ፣ ግጭት ማስቀረት፣ በመከላከል ሉዓላዊነትን ማስጠበቅና ከድል በኋላ አሸናፊነትን ማዝለቅ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሚገነባው ለሀገራችን ብቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የቀጣናውን ውስብስብ ችግሮች ታሳቢ አድርጎ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በህዝብ ብዛት፣ በቆዳ ስፋት፣ የቀጣናው ታላቅ ወንድም መሆኗን ገልጸው፤ የቀጣናውን ደህንነት ለመጠበቅ  ለወንድሞቻችን እገዛዋን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ የታላቅነት ሚናዋን ለመወጣት ቀጣናው ችግር ሲገጥመው ማገዝ በሚያስችል አቅም ተቋም እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የታጠቀችውን ሱ-35 ተከትሎ አንዳንድ በቅርብ ርቀት ላይ ያሉ ሀገራት ልታጠቃን ነው የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረው፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሱ - 35 የታጠቀችው ቀጣናው ካለበት የተዘበራረቀ ሁኔታ ለመከላከል እንጂ ማንንም ለማጥቃት አይደለም ብለዋል።

ይሁን እንጂ የምንታጠቃቸው ተዋጊ አውሮፕላኖችና የአየር መቃወሚያ ስርዓቶች ጥቃት ቢሰነዘርብን ለመከላከልና ጎረቤት ሀገር ቢጠቃ ድጋፍ ለመስጠት መሆኑን ወዳጅም ጠላትም ሊያውቀው እንደሚገባ ገልጸዋል።

የመከላከያ ሰራዊት የጠላትን ኢላማ ቀድሞ የማወቅ፣ የማየት፣ የማድረግ አቅማቸውን የማንኮታኮት ብቃቱ የሚመሰገን መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ቀጣናው ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ አሁንም መተኛት አያስፈልግም፤ ብዙ መሮጥ፣ ብዙ መትጋት፣ ውጊያን የማሳጠር አቅማችንን ማሳደግ አለብን ብለዋል።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ማንንም ሀገር ወርራ አታውቅም፤ ወደፊትም ፍላጎት የላትም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር መጥቶ ኢትዮጵያን የወረረ በክብር እንደማይመለስ ገልጸዋል።

ይሄ በጂኦግራፊ የታጠረ ጉዳይ አይደለም፤ ማንንም ይመለከታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬም የዓድዋ አባቶች አስደናቂ ተግባር ይደገማል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ራሷን የምትቆጥረው እንደ ታላቅ ወንድም ለአካባቢው ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ ይሄንን በተለያዩ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዋ አሳይታለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሚያኮራ ቁመና ላይ መሆኑን በመጥቀስ፤ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ባለሙያዎችን እያሰለጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም