ቀጥታ፡

አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቤቶችን መግዛት እንዲችሉ ከባንኮች ጋር የተሳሰረ የሞርጌጅ ፋይናንስ ሥርዓት በቅርቡ ይጠናቀቃል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቤቶችን መግዛት እንዲችሉ ከባንኮች ጋር የተሳሰረ የሞርጌጅ ፋይናንስ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በመደበኛ ጉባኤው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ያቀረቡትን የ2019 ዓ.ም የመንግሥት ዕቅድ መነሻ በማድረግ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠት ላይ ይገኛሉ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት በማብራሪያቸው እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በተለያዩ ክልሎች እየተገነቡ ናቸው፡፡

የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቤት ግንባታ ዕቅድ ከጉባ ብስራቶች መካከል አንዱ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ዕቅዱን እውን ለማድረግ የሚያስችል ከፍተኛ ዝግጀት ሲደረግ መቆየቱን አብራርተው፤ ፖሊሲ መጽደቅ፣  የፋይናንስ የሞርጌጅ ሥርዓት መፍጠርም ፣ የመሬትና ቴክኖሎጂ ዝግጀት መደረጋቸውን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ቤትን በፍጥነት መገንባት የሚችሉ የቱርክ፣ የቻይና፣ የኮሪያ ቴክኖሎጂዎች ላይ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እንዲሁም ቪላ ቤቶችን መገንባት የሚያስችሉ ፋብሪካዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቤቶቹን መግዛት እንዲችሉ ከባንኮች ጋር የተሳሰረ የሞርጌጅ ፋይናንስ ሥርዓት እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ዝግጅቱ በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም