ቀጥታ፡

የትውልድ ስልጣኔን ለማጽናት የጋራ የመጓዣ አቅጣጫ መንደፍና በመደመር መጓዝ ወሳኝ ነው 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦የትውልድ ስልጣኔን ለማጽናት የጋራ የመጓዣ አቅጣጫ መንደፍና በመደመር መጓዝ ወሳኝ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ያቀረቡትን የ2019 ዓ.ም የመንግሥት ዕቅድ መነሻ በማድረግ ከምክር ቤት አባላት ለተነሡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው ፤ ለውጡ ሲመጣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ግንኙነት በርከት ያሉ ውዝፍ ዕዳዎችና የማኅበራዊ ካፒታል መሸርሸር እንደነበር ገልጸዋል።

ይህንን ለመቀየር የተከናወኑ ሪፎርሞች ያስገኟቸውን ልምዶችና ትምህርቶች በመቀመር ከመንግሥትና ከትውልድ የሚሻገር ለልጅ ልጆች መሠረት የሚጥል የሥልጣኔ ጉዞ ለመጓዝ የሚያስችል ታላቁ የመደመር ሥልጣኔ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ስትራቴጂው እንደ ሀገር ያለንበትን ሁኔታ፣ ያለንን ሀብትና ዕምቅ አቅም በዝርዝር እንደሚያጠና የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካም ሆነች ኢትዮጵያ ትልቅ ሀብት ቢኖራቸውም ዜጎች ድሃ የሆኑበትን ሁኔታ በመቀየር ዜጎችን ሀብታም ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ ትኩረት መደረጉን አመላክተዋል።

ያለን ዕምቅ አቅም ወደ ድርጁ በመቀየርና የኃይል ቬክተር በማካሄድ ወደ ሀገራዊ ኃይል መለወጥ እንደሚገባ፤ እንዲሁም ካፒታል እንዴት እንደሚመጣና እንደሚተዳደር የሚያሳይ የኢኮኖሚ አርክና የኮንቨርጀንስ ሥርዓት በስትራቴጂው መካተቱን ገልጸዋል።

ልማት ማምጣት ብቻ ሳይሆን ያመጡትን ማጽናትና መምራት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ የተረከቡትን ነገር በጊዜው ለማስተላለፍ ዝግጁ መሆንና እንደ ባለአደራ በመቁጠር መሥራት የሚያስችል የባለአደራ አስተሳሰብ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።

ተቋማትን፣ ሲስተሞችንና አቅሞችን የሚገነቡ 15 ሞዴሎች መቀመጣቸውን ገልጸው፤ የሁሉም ነገር መሠረት መደመር መሆኑንና እያንዳንዱ ዜጋ ከራሱ ደረጃ ወደ ሚልቀው ደረጃ እንዲሸጋገር የሚያግዝ መሣሪያ እንጂ የአንድ ፓርቲ ሂሳብ እንዳልሆነ አብራርተዋል።

የአሁኑ ትውልድ እየገነባ ጣራ ላይ የሚቀመጥ ገንቢ ትውልድ መሆኑን ገልጸው፤ አንድ መንግሥት ለ25 ዓመት እንደማይቀጥል ቢታወቅም የ25፣ 50፣ 75 እና 100 ዓመታት የጋራ የመጓዣ አቅጣጫ መንደፍ ግድ እንደሚል አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም