የመከላከያ ሰራዊት በግልጽ ርዕይ፣ ቀጣይነት ባለው ትጋትና በጠንካራ ተቋማዊ መሠረት እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሰራዊት በግልጽ ርዕይ፣ ቀጣይነት ባለው ትጋትና በጠንካራ ተቋማዊ መሠረት እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በግልጽ ርዕይ፣ ቀጣይነት ባለው ትጋትና በጠንካራ ተቋማዊ መሠረት በቀላሉ ሊናወጥ በማይችል ደረጃ እየተገነባ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በመገኘት ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ኢትዮጵያ ታሪክ ጠገብ እና ጠንካራ ሀገር መሆኗን አውስተዋል።
በዚህ ጥንካሬዋ ምክንያት ባህሏን፣ ማንነቷን፣ ሀገራዊ ስያሜዋን ይዛ ለዘመናት መዝለቅ የቻለችው ከፈተና እና ከወጀብ ውጭ እንዳልነበር ጠቁመዋል።
ሀገራችን በግራም በቀኝም በርከት ያሉ ፈተናዎች እያጋጠማት እንደነበር ገልጸው፤ ነገር ግን በየዘመኑ አቅሙ ቢለያይም በተደራጀ ሕዝብ፣ ሠራዊት እና በማህበረሰቡ የተባበረ ልብ እንደ ሀገር ለመጽናት የሚያስችል ቁመና ያላት ትልቅ ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል።
ይሄ ትልቅነት እና ታሪክ ግን በነፃ የመጣ አለመሆኑን ገልጸው፤ መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን በነፃ ሊገብሩ የፈቀዱ፣ አባቶችና እናቶች ስለነበሩን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በግልጽ ርዕይ፣ በቀጣይነት ባለው ትጋትና በጠንካራ ተቋማዊ መሠረት በቀላሉ ሊናወጥ በማይችል ደረጃ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፤ የመገንቢያ አቅጣጫዎች አንደኛው ራስን መቻል መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ላይ ተቋሙ የራሱን ምግብ፣ የራሱን ልብስ፣ የራሱን ተተኳሽ በበቂ ማምረት የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁለተኛው ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ጠንካራ አቅም መገንባቱን ተናግረዋል።
ሦስተኛው ሥልጠና መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ከራሱ አልፎ ለሌሎች ሀገራትም አቅም መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል።
አራተኛው አምራችነት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ባለፈው ዓመት መከላከያ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት ምርት ለውጭ ገበያ መላኩን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ጥይት፣ ድሮን እና የአውሮፕላን ጥገናዎች ከፍተኛ ገቢ እያስገኙ መሆኑን ጠቁመው፤ ራሱን እየደገፈ አምራች እየሆነ የሚሄድበትን መንገድ ለመከተል መሞከሩን አንስተዋል።
በዚህም በከፍተኛ ደረጃ ተቋሙ እየተገነባ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የሀገር መከላከያ ቀጣናው ችግር ሲገጥመው ወንድሞቹን ለማገዝ በሚያስችል ደረጃ ዝግጅት እያደረገ ያለ ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የታጠቀችው ቀጣናውን ለመከላከል እንጂ ማንንም የማጥቃት ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መከላከያ ሰራዊትን የሚያከብር፣ የልጆቹን ደም የሚያከብር፣ የሚያሰማራውን ጦር ዋጋ መክፈል እውቅና የሚያደርግ ምክር ቤት በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ መከላከያ ሰራዊቱ ለሚከፍለው ዋጋ እውቅና አለመስጠት መጥፎ ልምምድ መሆኑን አስገንዝበዋል።