የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በዘመናዊ የአመራር ሥርዓት እየተመራ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በዘመናዊ የአመራር ሥርዓት እየተመራ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በዘመናዊ የአመራር ሥርዓት እየተመራ ያለ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በመገኘት ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊና የተቀናጀ ፕሮጀክት መሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ የቤቶች ግንባታና ሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች የመቻል አቅማችን ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አቅም አላት፣ የማድረግ አቅማችን ጨምሯል፤ ዓለም የሰራውን እኛ መሥራት አይሳነንም የሚል የፀና አቋም አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አትችሉም የሚለው ዕድገታችንን የማይፈልጉ ሀገራትና የገዟቸው ባንዳዎች አጀንዳ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የፕሮጀክቱን ግንባታ ማየት በራሱ አስተማሪ መሆኑን በማንሳት፤ አራት ሺህ የሚጠጉ ትራኮች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ታግዘው በአንድ ውስን ሥፍራ የሚንቀሳቀሱበት አስደናቂ የአስተዳደር አቅም የሚታይበት መሆኑን ገልጸዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የመጀመሪያ የቦታ ዝግጅት ሥራ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት በተያዘለት እቅድ ይጠናቀቃል ብለዋል።
የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ ግንባታ ጨረታ በሂደት ላይ በመሆኑ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውጤቱ እንደሚታወቅ ገልጸዋል።
የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ፋይናንስና የማስፈጸም ብቃት ስለሚፈልጉ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የምክር ቤቱና የህዝቡ ድጋፍ ከታከለበት ሁሉም በተያዘላቸው ጊዜ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።