ቀጥታ፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብና ኮይሻን የመሳሰሉ ግዙፍ ግድቦችን በአጭር ጊዜ ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃት ታላቅ የልማት እመርታ ነው 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ እንደ ታላቁ ህዳሴ ግድብና ኮይሻ ያሉ ግዙፍ ግድቦችን በጥቂት ዓመታት ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃት ታላቅ የልማት እመርታ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ዛሬ 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በመደበኛ ጉባኤው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2019 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ያቀረቡትን የ2019 ዓ.ም የመንግሥት ዕቅድ መነሻ በማድረግ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተነሡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት፤ የኢንዱስትሪ ዋና ግብዓት ኢነርጂ መሆኑንና በዚህ ላይ ሰፊ ሥራዎች በመሠራት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

በዚህም በአፍሪካ አንደኛ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ሁለት ሺህ ሜጋ ዋት በማመንጨት በአፍሪካ ሦስተኛ የሆነው ኮይሻ ኃይል ማመንጫ ሀገሪቱና ኢንዱስትሪዎች የተሟላ ኃይል እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው አንስተዋል፡፡

በዚህ ዓመት የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ከሞላ ጎደል ሊጠናቀቅ እንደሚችልና ኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ወደ ቀጣይ ዓመት ሊሸጋገር እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ እንደሚመረቅ አስታውቀዋል፡፡

ይህም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ታላቁ ህዳሴን እና ኮይሻን የሚያካክሉ ትላልቅ ግድቦች ሠርቶ ጥቅም ላይ ማዋል ለኢትዮጵያ ትልቅ እመርታ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይም የሲሚንቶ ምርት ለማሳደግ በተሠራው ሰፋፊ ሥራ ምርቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ማስቻሉን አብራርተዋል፡፡

በድንጋይ ከሰል፣ ብረት፣ ሴራሚክስ፣ መስታወት እና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም የውጭ ምርት በሀገር ውስጥ መተካት የተቻለበትና ለውጭ ምርት ይወጣ የነበረውን ስድስት ቢሊየን ዶላር በሀገር ውስጥ መሸፈን መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም