የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የመንግሥትን ሀብት ከብክነት በማውጣት ወደ ትርፋማነት አሸጋግሯል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የመንግሥትን ሀብት ከብክነት በማውጣት ወደ ትርፋማነት አሸጋግሯል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 17/2019 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የመንግሥትን ሀብት ከብክነት በማውጣት ወደ ትርፋማነት ማሸጋገሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በመገኘት ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ለማጠናከር የገቢ መሠረቶችን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ሕዝብ የመሠረተ ልማት ፍላጎት ከጥቂት ሰዎች በሚሰበሰብ ገቢ ብቻ ማሟላት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአርሶ አደሩ ወቅቱን የጠበቀ የግብርና ግብዓት ለማቅረብ ለመሠረተ ልማት ግንባታ የሚውል የገቢ ግብር መክፈል አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ የነበረውን የዕዳ ጫና ወደ መካከለኛ ማውረድ ተችሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመንግሥት ኩባንያዎች ሚናቸው ከፍ ያለ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመንግሥትን ሀብት ከብክነት በማውጣት ወደ ትርፋማነት በመቀየር ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
ከዓመታት በፊት ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል ይቸገሩ የነበሩ እንደ ወንጂ ስኳር ያሉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነበረበት 2 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር አጠቃላይ ሀብት ከሦስት እጥፍ በላይ በማሳደግ ወደ ዘጠኝ ትሪሊዮን ብር አድጓል ብለዋል።
ከሀብት ማሰባሰብ ባለፈ በዓመት 778 ቢሊዮን ብር ገደማ ገቢ ያስገኝ ከነበረበት ወደ 3 ነጥብ 1 ትሪሊዮን ብር ማደጉን ገልጸዋል።
ለመንግሥት የሚከፍለው ግብር ከ17 ቢሊዮን ብር ወደ 316 ቢሊዮን ብር ማደጉን ገልጸው፤ ዋና ግብር ከፋዮች የመንግሥት ኩባንያዎች ሆነዋል ብለዋል።
መንግሥት ባለፈው ሩብ ዓመት ከሰበሰበው 454 ቢሊዮን ብር ገደማ ገቢ 153 ቢሊዮን ብሩ የተሰበሰበው ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ወርቅ ማጣሪያ፣ ማዳበሪያ እና በመሳሰሉት አዳዲስ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ በሩብ ዓመቱ 72 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ የኢትዮጵያን ሀብት ከብክነት በመታደግ ሰብሰብ አድርጎ ወደ ልማት ቀይሯል ብለዋል።