ቀጥታ፡

በልማት የምትፈጥን፣በሰላም የምትጸና፣በዓለም የምትደምቅ ኢትዮጵያ!

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የያዘችውን ራዕይ በተጨባጭ ሥራዎች እየገለጠች ትገኛለች።የመደመር መንግሥት ዘርፈ ብዙ ፖሊሲዎች የሀገሪቱን እምቅ ሀብት በመጠቀም የዜጎችን ሕይወት ለመለወጥ እና የሀገርን ሉዓላዊነትና ክብር ከፍ ለማድረግ ያለሙ ናቸው።

ይህ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ የመንግሥት ተቋማት፣የግሉ ዘርፍ እና የመላው ሕዝብ የተቀናጀ ርብርብ የሚታይበት ታሪካዊ ጉዞ ነው።

በኢኮኖሚ እና በመሠረተ ልማት መስክ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በከተማ ልማት ዘርፎች ፈጣን እድገት እየተመዘገበ ይገኛል።በስንዴ ልማት እና በሌማት ትሩፋት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተወሰዱ እርምጃዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር አፋጥነውታል።

በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጨት ሥራ እና በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማቶች የኢኮኖሚ መነቃቃቱን እና የከተሞችን ዘመናዊነት በግልጽ ያሳያሉ።


 

ዘላቂ እና አስተማማኝ እድገት ለማረጋገጥም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሰፊ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።በዚህ ረገድ ሀገራዊ ምክክሩ በኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ያሳየ ሆኗል።

በውጭ ግንኙነት መስክ ደግሞ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር እና በኮንፈረንስ ዲፕሎማሲ የጎላ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች።በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያበረከተችው አስተዋጽኦ እና የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ ዓለም አቀፍ ተሰሚነቷን ከፍ አድርጎታል።

በተጨማሪም አዲስ አበባ ታላላቅ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎችን፣በብቃት ማስተናገዷ የዲፕሎማሲ ልዕልናዋን እና የገጽታ ግንባታ ስኬቷን በዓለም ፊት አጉልቶ አሳይቷል።በአዲስ አበባ የሚካሄደው ኮፕ 32ትም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ከፍታ በተግባር የሚያሳይ ይሆናል።


 

እነዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ተደማምረው ሀገሪቱን በልማት የምትፈጥን፣ በሰላም የምትጸና እና በዓለም አቀፍ መድረክ የምትደምቅ ኢትዮጵያ እያደረጓት ይገኛሉ።

የልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ፣ ኢትዮጵያ ለዜጎቿ የምትመች እና ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ተምሳሌት የምትሆን የበለጸገች ሀገር የመሆን ራዕይዋን በተግባር እያረጋገጠች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም